በእጣን እና ሙጫ ምርት ከ5 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

6

 

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእጣን እና ሙጫ ምርት ለ5 ሺህ 403 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።

ወይዘሮ ትዕግስት ዓለሙ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 04 የገበያ ማዕከል ጭስ ሲገዙ አግኝተናቸዋል። በፊት አንድ ኪሎ የተቀመመ ጭስ በ200 ብር ሒሳብ እገዛ ነበር አሁን ላይ በ1 ሺህ ብር ሒሳብ ነው የምገዛው ብለውናል። ቡና በጣም እንደሚወዱ እና ጭስ ካልተጨሰ ደግሞ የጠጡ እንደማይመስላቸው አጫውተውናል። እናም የአስቤዛየ አንድ አካል አድርጌ እገዛዋለሁ ነው ያሉት።

የተለያዩ የጭሳ ጭስ አይነቶችን ሲሸጡ ያገኘናቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነጋዴ የጭስ ዋጋ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

እኛ ከውጭ ከሚያስመጡ ነጋዴዎች ነው የምንገዛው ያሉት ሻጩ አንድ ኩንታል ከርቤ እጣን እስከ 120 ሺህ ብር ድረስ እንደሚገዙ ነው የተናገሩት። በዚህም ምክንያት ለተጠቃሚው ዋጋው መወደዱን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ የሚመረተው እጣን ከውጭ የሚገባውን ጭስ ከማስቀረት እና ለማኅበረሰቡ ተመጣጣኝ በኾነ ዋጋ ከመሸጥ አንጻር ያለው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል የሚለውን ጥያቄ አሚኮ ለነጋዴው አቅርቧል። የሀገር ውስጥ እጣን ከውጭ ከሚገቡ ጭሶች በላይ ዋጋው ከፍ እንደሚል እና ወደ ውጭ ስለሚላክ የገበያ እጥረት መኖሩንም መልሰውልናል።

አንድ ኩንታል የሀገር ውስጥ እጣን እስከ 160 ሺህ ብር እንደሚገዙም ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል የሚገኘው ወልቃይት–ጠገዴ–ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ የእጣን እና ሙጫ የደን ሃብት ባለቤት ነው።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ በጥናት ያልተደገፈ ቢኾንም ከ70 እስከ 80 ሺህ ሄክታር የሚደርስ መሬት በእጣን እና ሙጫ ዛፎች ተሸፍኗል ብለዋል።

ነገር ግን ይህ የተፈጥሮ ሃብት ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ገብቷል ለማለት እንደማያስችል ነው የተናገሩት።
ከዚህ በፊት በነበረው መንግሥት ሃብቱ በማኅበራት፣ በሽርክና እና በግል ባለሀብቶች እጅ እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን ለይ ደግሞ ያሉ ማኅበራት ያለ አዲስ ጥናት ቀጥለው ሥራ ላይ መኾናቸውም ገልጸዋል። ሃብቱን በሕገ ወጥ መንገድ የሚጠቀሙ አካላት መኖራቸው ችግር መኾኑንም ጠቁመዋል።

በዘርፉ ከዓመት ዓመት የሚታይ የምርት መጠን ጭማሪ እንዳለ የተናገሩት ኀላፊው ነገር ግን በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ ሙሉ አቅሙን እንዲጠቀሙ እንዳላስቻላቸውም ገልጸዋል።

ዘርፉ በተጠናከረ አሥተዳደር ከተሠራበት ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እና ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድጋፍ ሊያበረክት ይችላል ነው ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ መምሪያው ከዞን አሥተዳደሮች እና ከወረዳ መሪዎች ጋር በመተባበር ሥራ አጥ ወጣቶችን በማሠልጠን እና ሕገ ወጥ አምራቾችን በመቆጣጠር ዘርፉን በስፋት ወደ ልማት ለማስገባት ጥናት እያካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ በተለይ ቃብቲያ ሁመራ እና ወልቃይት ወረዳዎች የእጣን እና ሙጫ ምርት በከፍተኛ መጠን የሚመረትባቸው እንደኾነም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የደን ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር ተፈራ አካሉ በክልሉ ውስጥ ያለው የእጣን እና ሙጫ ሃብት በተደራጀ አሥተዳደር እንዲጠበቅ እና እንዲለማ በርካታ ተግባራዊ ሥራዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።

የእጣን እና ሙጫ ደኑ በባለቤትነት እንዲጠበቅ ማኅበረሰቡ በተለይም ወጣቶች በአሳታፊ የደን አሥተዳደር (PFM) ስር ተደራጅተው እየሠሩ እንደኾነ አንስተዋል። በዚህም ወጣቶች ሥልጠና ተቀብለው ወደ ሥራ በመግባት ደኑን እየጠበቁ ምርት በማምረት ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።

በዚህ ዘርፍ ብቻ ለ5 ሺህ 403 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋለ።

በክልሉ ከ450 ሺህ ሄክታር በላይ የእጣንና ሙጫ ደን ሽፋን እንዳለም መረጃዎች ያሳያሉ።

በየዓመቱም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የእጣን እና ሙጫ ምርት እየተመረተ እንደኾነም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር በሴቶች እኩልነት እና ነጻነት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።
Next article” የሴቶች ቀን መከበሩ የሴቶችን የፓርላማ ተሳትፎ አሳድጓል” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)