“አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን ብቃት ላይ ነች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

13

ባሕር ዳር፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካ የራሷን አጀንዳ የመቅረጽ እና የማስተዳደር ሙሉ አቅም ላይ መኾኗን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አህጉሪቱ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ መኾኗን ጠቁመው የተፈጥሮ ሃብትን ለጋራ ዕድገት እና ለቀጣናዊ ትስስር የመጠቀም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት አድርገዋል።

ውኃ እንደ ተራ ሃብት ብቻ ሳይኾን እንደ ልማት መሣሪያ፣ የፈጠራ መነሻ እና ለቀጣናዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ለከተሞች ዕድገት፣ ለግብርና፣ ለጤና እና ለጠቅላላ ሰላም ወሳኝ ቁልፍ መኾኑንም አስምረውበታል።

ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን ለልማት ማፋጠኛ እየተጠቀመች መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ አብነት አንስተዋል።

ግድቡ በአሁኑ ወቅት ለመኖሪያ ቤቶች እና ለኢንዱስትሪዎች ኀይል ማቅረብ መጀመሩን ገልጸው ለጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል በማጋራት ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይህ ስኬት አፍሪካውያን የጋራ ሃብታቸውን በፍትሐዊነት ተካፍለው ለጋራ ዕድገት እንዴት መሥራት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ መንግሥታት ለጋራ ብልጽግና በቁርጠኝነት የሚሠሩ ከኾነ አህጉራዊ ወንዞች የክርክር ምንጭ መኾናቸው ቀርቶ ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ዋነኛ መሣሪያ እንደሚኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አሳስበዋል።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብር የዜጎች አርበኝነት የሚገለጽበት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleቡሩንዲ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርነትን ተረከበች።