“የሰላም አማራጭን መከተል የስልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ ነው” ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

15
ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በባሕር ዳር መክሯል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት ሰላም ሀገራዊ ዕድገትን ለማምጣት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ቅቡልነት ላለው ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ነው።
የሰላም አለመኖር በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መኾኑን ጠቁመዋል። ይህም በተግባር የታየ ነው ብለዋል።
የሰላም ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይኾን የሕዝብ ጥያቄ በመኾኑ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ነው ያሉት። ሰላምን ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ማኅበረሰብ ሊሳተፍበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰላም አማራጭን መከተል የስልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ መኾኑን በመገንዘብ በጫካ ያሉት ኃይሎች ሰላምን እንዲመርጡ በማድረግ ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ትዝታ የኔዓለም በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ምክክር እና ውይይት የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል።
ከኃይል አማራጭ ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን መከተል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዋና ተዋናይ ሊኾኑ እንደሚገባ አንስተዋል።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ታዬ እንደገለጹት ሰላም የሚጀምረው ከግለሰብ ነው። የሰላም መጥፋት ሁሉንም እንደሚጎዳ ሁሉ የሰላም መምጣትም ሁሉንም የሚጠቅም ነው ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሃይማኖት ተቋማት ሰፊ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። አሁን እየታየ ላለው አንጻራዊ ሰላም የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸው የጎላ መኾኑን አንስተዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next articleፈረሶቹ ጋላቢዎቻቸውን፣ ጋላቢዎቹም ፈረሶቻቸውን ያውቃሉ።