
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥም የሕዝብ ተወካዮች የድርሻቸውን ሲወጡ ቆይተዋል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ትላልቅ የልማት እቅዶችን ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ የጠቀሱት አፈ ጉባኤዋ የምክር ቤት አባላትም ሕዝብን በማነቃነቅ ለልማቶች መፈጸም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዘላቂ ሰላም የልማት መሠረት ነው፤ በዚህም መሠረት የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን እያደረገ ነው ብለዋል። ሁሉም በአንድነት ከሰላም ጎን መቆም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
አሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ መፈለግ ከፍላጎት ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ የክልላችን የሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ጉዞ ህያው ማሳያ ነው ሲሉም ዋና አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።
“ሕዝባችን ከዚህ በኋላ የእርስ በእርስ ግጭትን ለመሸከም አይፈቅድም” ሲሉም ተናግረዋል። የሚያሻግረን የሰከነ ውይይት እና ንግግር ነውና የግጭት ሀሳብን ያነገበ ሁሉ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የቆመ መኾኑን በመገንዘብ ሰላሙን መምረጥ ይገባዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
