“የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተሳካ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

3
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የተናገሩት የ2030 ዲጂታል ስትራቴጂ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ጋር ባደረጉት “የእሳት ዳር ወግ” የሚል ሥያሜ በተሰጠው ላይ ውይይት ነበር።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢትዮጵያ የመከወን ብቃት የታየበት መኾኑንም ገልጸዋል። መነሻውን የ2025ቱን ስትራቴጂ ያደረገው እና በይፋ የተጀመረው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሦስት መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ የተመሠረተ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እነዚህ ፍላጎቶች ሁሉም ዜጎች ባሉበት ኾነው በስልካቸው አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር የሚያስችል ተደራሽነት፣ በፆታ፣ በአካል ጉዳት ወይም በሌሎች ተጽዕኖዎች ምክንያት ዜጎች ሊያገኙት የሚገባውን ዕድል እንዳያጡ የሚያደርግ እኩል ዕድል መፍጠር እና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና በዜጎች መካከል መተማመን መፍጠር የሚሉ መኾናቸው በውይይቱ ተገልጿል።
እነዚህ ሦስቱ ተደምረው የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የሀገር ዕድገትን ማምጣት እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚችሉ መኾን እንዳለባቸውም አብራርተዋል።
ዲጂታል 2030 ላይ በትኩረት የሚሠራው በዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት (DPI) ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ውስጥ ዋና ዋና ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ ፋይዳ መታወቂያ አንዱ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
የሳይበር ደኅንነት፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል ሉዓላዊነት ላይም ሰፊ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
የዚህ ስትራቴጂ መጀመር ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር የሚያፋጥን ወሳኝ እርምጃ ለመኾኑ ማሳያ፣ ዜጎች ያለምንም እንግልት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል እና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚችል ቁርጠኝነት የታየበት ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበእንስሳት ሃብት ልማት ውጤት ማምጣት ተችሏል።
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ።