ስለምንስ የእናቶችን እንባ እና ሀዘን የሚሰማ ጆሮ ጠፋ?

4
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች ዘካሪ እና መካሪ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት በሚል መሪ ቃል በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ እየተወያዩ ነው።
በውይይት መድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው። የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በሰከነ ውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እና በሙሉ አቅም ወደ ልማት ለመግባት ያለመ ውይይት ነው እየተካሄደ ያለው።
የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥረት እያደረጉ ነው። ምክር ሰምተው የሚመለሱ እንዳሉ ሁሉ የሀገር ሽማግሌን ምክር የማይቀበሉ እና ከእሴት ያፈነገጡ እንዳሉም ጠቁመዋል።
ይባስ ብሎም የሀገር ሸማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ጭምር የሚያዋክቡ እና ለግድያ የሚያንገራግሩ ታጣቂዎች እንደገጠሟቸውም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በሰላም እያረሱ አይደለም፤ ነጋዴዎችም እንደልብ አይዘዋወሩም፤ እናቶች እና ሕጻናትም ነገ ምን ይገጥመን ይኾን እያሉ የዘወትር ጭንቀት ላይ ናቸው ብለዋል። እንደ ሀገር ሽማግሌነታቸው ስለ ሀገር ዝም እንደማይሉ እና አሁንም ቢኾን ለእርቅ እንደሚጥሩ ገልጸዋል።
ከሀገር ወግ እና ባሕል ወጥተው የሀገር ሽማግሌዎችን የእርቅ ልመና የሚገፉ ሲገኙ ደግሞ ሕዝብ ሰላም ውሎ ያድር ዘንድ መንግሥት የራሱን አማራጭ ወስዶ ሕግ እንዲያስከብር ጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባቶችም መንግሥት ለታጣቂዎች የሰላም ጥሪ ማድረጉ መልካም መኾኑን ጠቅሰው አሁንም ቢኾን በተለየ መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሰላም የሁሉም መሠረት ነው፤ ሰላም በተጓደለ ጊዜ ወደቤተ እምነት ለመድረስም ይቸግራል ነው ያሉት። የሁሉም ሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም ያስተምራሉ፤ ይሰብካሉ፤ ለመሸምገልም ይጥራሉ ነው ያሉት።
ለሀገር ሰላም ሲሉ ግፍን ተጸይፈው “ሕዝቤን አደራ” ብለው ያለፉትን አቡነ ጼጥሮስን አርዓያ በማድረግ እስከ መስዋዕትነት የሚዘልቅ የሰላም ልመና እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። ለሰላም ዋጋ ሊከፍሉ የሚችሉ የሃይማኖት አባቶች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይመረጡ እና በጋራ ኾነን ለእርቅ እና ለሰላም እስከመጨረሻው እንጓዛለን ነው ያሉት።
መንግሥት አሁንም ቢኾን ይቅርታውን ይቀጥል ብለዋል። ግጭት የወለደው የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ፈትኖታል፤ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሠርቶ የዕለት እንጀራ ማግኘትም ኾነ ልጅ ማሳደግ ከባድ ኾኖብናል ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች።
ታጣቂዎች ስለምን የሕዝባቸውን ስቃይ አልተገነዘቡም፤ ስለምንስ የእናቶችን እንባ እና ሀዘን የሚሰማ ጆሮ አጡ? ሲሉ አጠይቀዋል።
አሳዛኝ የኾኑ ግድያዎችን እየተለማመድን ነው፤ እናት እና አባቶች ይሄን ሳላይ በሞትኩ እያሉ ነው፤ ፈጥነን ከግጭት እንውጣ ብለዋል ተወያዮች።
የአማራ ክልል ሕዝብ በውል የሚታወቁ ጥያቄዎች ነበሩት፤ ልጆቻችንም የሕዝብን ጥያቄ አስመልሳለሁ ብለው ሲወጡ እውነት መስሎን ነበር ብለዋል ተሳታፊዎች።
ይሁን እንጅ ልጆቻችን መልካቸውን ቀየሩ፤ ከሀገር እና ከሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተሰልፈው አሳዘኑን ነው ያሉት። የእነዚህ ልጆች ወላጆች ልጆቻቸውን ይምከሩ፤ ዘመዶቻቸውም ቤተሰባዊ ትግል አድርገው ወደ ሰላም ይመልሷቸው ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕንድ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ።
Next articleበሁሉም አማራጮች እርስዎን ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ ነን!