
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለመሻት እንደተመሠረተ የሚነገርለት ጣና ፎረም ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው ውይይት በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
“አፍሪካ በተለዋዋጭው የዓለም ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት በተጀመረው ፎረም ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ” ጣና ፎረም ለእኛ ከሁነትም በላይ ነው” ብለዋል።
ፎረሙ አፍሪካ በተለዋዋጭው ዓለም የሚመጡ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ከቀሪው ዓለም ጋር እኩል ለመራመድ በጋራ የምትመክርበት፣ የአሕጉሩን ሰላም፣ እድገት እና ብልጽግና በበጎ የምትተልምበት መድረክ መኾኑን አንስተዋል።
ፎረሙ በፍጥነት እያደገ እና እየተለዋወጠ የመጣውን የቴክኖሎጅ ተጽዕኖ በመቋቋም አሕጉሪቷ ያላትን ጸጋዎች ለመጠቀም የሚያስችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ይንሸራሸሩበታል ነው ያሉት።
አፍሪካ የወጣቶች ጉልበት ተስፋ ያላት፣ የታሪክ፣ የባሕል፣ የፈጥሮ ሃብት እና እሴት ባለቤት መኾኗንም አንስተዋል። እነዚህን ጸጋዎች አቀናጅቶ ለማልማት እና ለመለወጥ ፎረሙ ዓይነተኛ ሚና አለውም ነው ያሉት።
ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው እንደ አዘጋጅ ቆይታችሁ ምቹ እና ውይይታችሁ ስኬታማ እንዲኾን በበቂ ተዘጋጅተናል ብለዋል። ባሕር ዳር ተፈጥሮ ያስዋባት፣ ጣናን በራስጌዋ እና የምድራችን ታላቅ ወንዝ ዓባይን በግርጌዋ የታቀፈች ውብ ከተማ ናትና ተዘዋውራችሁ እንድትጎበኙ ጋብዘናችኋል ነው ያሉት።
ለፎረሙ ስኬታማ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሠሩ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በፎረሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን (ዶ.ር) ጨምሮ፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን፣ የሀገራት እና የድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
