
ባሕር ዳር:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ፍረም ከዛሬ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተጉዘው ከትላንት ጀምሮ ወደ ባሕር ዳር ከተማ መግባታቸውን ቀጥለዋል።
ዛሬ ጠዋትም እንግዶቹ እየገቡ ሲኾን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው እንግዶችን በክብር እየተቀበሏቸው ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የእንግዶች መምጣት ለተነቃቃው የባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግብዓት እንደሚኾንም ገልጸዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ በልማት ላይ ትገኛለች፣ ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ አቅሟም የበለጠ እያደገ ነው ብለዋል።
የጣና ፎረም እንግዶችን በመቀበል በባሕር ዳር ሕዝብ የእንግዳ አቀባበል እሴት ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት።
ጣና ፎረም ለባሕርዳር ኢኮኖሚ መነቃቃት ተጨማሪ ዕድል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በምቹዋ ከተማ ማልማት የሚፈልጉ ባለሃብቶችም ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ጋብዘዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
