
አዲስ አበባ: መስከረም 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወጋገን ባንክ 32ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የወጋገን ባንክ የቦርድ ሠብሣቢ አብዲሹ ሁሴን ባንኩ እ.ኤ.አ በ2024/25 በጀት ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ የኾነውን 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል ብለዋል።
ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ38 በመቶ ዕድገት በማሳየት የአንድ አክሲዮን ትርፍ ወደ 46 ነጥብ 10 በመቶ ማደጉንም የቦርድ ሠብሣቢው ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ባንኩ ከታክስ በፊት በታሪኩ 3 ነጥብ 85 ቢሊዮን ትርፍ በማግኘት ካለፈው በጀት ዓመት የ73 በመቶ ብልጫ እንዳስመዘገበም አስታውቀዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ፋይናንስ እና ፋይናንስ ነክ ባልኾኑ የአፈጻጸም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንም ጠቅሰዋል፡፡
የባንኩ ባለአክሲዮኖችን ወደ 14 ሺህ 871 ማሳደግ እንደተቻለም ተገልጿል። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል የ37 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እንዳሳየም ተጠቁሟል።
የባንኩን ካፒታል 7 ቢሊዮን በማድረስ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የባንኮች ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል መስፈርት በላይ ማድረግ እንደተቻለም ተናግረዋል።
የባንኩ ጠቅላላ ሃብትም ወደ 84 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማደጉንም የቦርድ ሠብሣቢው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና በሴቶች አካታችነት ዙሪያ ባደረገው ምዘና ወጋገን ባንክ ከ30 የግል ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ደረጃ መያዙንም ተናግረዋል።
ወጋገን ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አቶ አብዲሹ ጠቅሰዋል፡፡
ባንኩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ያለፈው በጀት ዓመት በባንኩ የታሪክ ምዕራፍ በጉልህ ስኬቶች የታጀበ እና በኢትዮጵያ የሠነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ላይ ቀዳሚ ኾኖ መመዝገቡንም አብራርተዋል።
ወጋገን ካፒታል የተሰኘ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የግል ኢንቨስትመንት ባንክን አቋቁሞ ወደ ሥራ በማስገባት ለካፒታል ገበያ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለበት ዓመት መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ የፖሊሲ ለውጦችን እና አዳዲስ መመሪያዎችን ከግምት በማስገባት የባንኩን ተወዳዳሪነት እና ዕድገት ማስቀጠል የሚያስችል የስትራቴጂ ሰነድ ዝግጅት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!