24ኛው የአማራ ክልል የባሕል ስፖርቶች ሻምፒዮና ውድድር በእንጅባራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ከኅዳር 13/2019 ዓ.ም እስከ ኅዳር 20/2019 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ገና፣ ኩርቦ እና ትግልን ጨምሮ በአስር የስፖርት አይነቶች ተካትተዋል።
በውድድሩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ በውቀት ገዛኸኝ የባሕል ስፖርቶች የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነፀብራቆች መኾናቸውን ተናግረዋል።
የቀደምት አባቶቻችን አርቆ የማሰብ፣ የአካል ብቃት እና የጀግንነት መንፈስ በባሕል ስፖርቶች ጎልተው እንደሚታዩ ያነሱት አቶ በውቀት ይህንን ጠቃሚ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የባሕል ስፖርት ዕድገት መሠረት የሚጥሉ በርካታ ባሕላዊ ስፖርቶች የሚከወኑበት መኾኑንም አንስተዋል።
ውድድሩ የሕዝቦች ታሪክ፣ ባሕል፣ ማንነት እና ትውፊታዊ እሴቶች የሚተዋወቁበት ብሎም ትልቅ ማኅበራዊ መስተጋብር የሚፈጠርበት መድረክ ነው ያሉት ደግሞ የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና መሬት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቅነህ በላይነህ ናቸው።
ከተማ አሥተዳደሩ ይህንን ስፖርታዊ ውድድር በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓልም ነው ያሉት።
ስፖርተኞች ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ በተወከሉበት የስፖርት ዘርፍ ውጤታማ ለመኾን እንዲሠሩም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_13_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



