በባንክ ኦፍ አሜሪካ የቀረበው የ2019 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር፣ አዲስ መልክ እየያዘች በምትገኘው አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
ይህ የአፍሪካ ታላቁ የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የመዲናዋን ዘመናዊነት እና ውበት ለዓለም ከማሳየቱም ባለፈ፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶች የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት እና የሩጫ ባሕል በቅርበት እንዲያዩት ዕድል የፈጠረ ነበር።
በውድድሩ ላይ የተሳተፉ የውጪ ሀገር ዜጎችም የሩጫው ዝግጅት፣ የሕዝቡ ስሜት እና በአዲስ መልክ የተዋበችው አዲስ አበባ ልዩ ትዝታ እንደፈጠሩባቸው ተናግረዋል።
ለረጅም ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ በመመላለስ ሕዝቡን የተላመዱት ኬንያዊው ኤልያስ ማኮሪ፣ የዘንድሮው ውድድር ከወትሮው የተለየ መኾኑን ጠቅሰዋል። “በርካታ ታላላቅ አትሌቶች በረገጡት መንገድ ላይ መጥቶ መወዳደር ልዩ ስሜት አለው” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት ሌላኛዋ ኬንያዊት ዶርካስ ሞየ በበኩላቸው ወደ ውድድሩ የሳባቸው ዋነኛ ምክንያት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች መኾናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለአራት ወራት መቆየታቸውን የገለጹት ቻይናዊው ሆን ቦ ዉ ደግሞ በሀገራቸው ቻይና ተመሳሳይ የሩጫ መድረኮች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያው ግን በሕዝቡ ድጋፍ እና በዝግጅቱ ጥራት እጅግ እንደሚልቅ መስክረዋል። ኢትዮጵያ “የሯጮች ሀገር” መኾኗን በዐይናቸው በማየታቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድርነቱ ባሻገር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እና የውጪ እንግዶችን በአንድነት በማሠባሠብ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክር መድረክ ነው።
ከሙዚቃ፣ ከጭፈራ እና ከኅብረ-ቀለም ጋር ተዋህዶ የሚካሄደው ይህ ሩጫ፣ አዲስ አበባን ለአንድ ቀን ወደ ትልቅ የደስታ እና የአብሮነት አደባባይ ይለውጣታል።
ውድድሩ ወጣት ሯጮች ከታላላቅ አትሌቶች ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ሁሉም የውጪ ተሳታፊዎች በጋራ የተስማሙበት ጉዳይ የመዲናዋ አዲስ አበባ ውበት ጎልቶ መውጣቱን እና ለጎብኚዎች ይበልጥ ምቹ መኾኗን ነው።
“ሩጫዬ ቀለሜ” በሚል መሪ መልዕክት ከ60 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ተሳታፊዎችን ያሳተፈው ይህ ውድድር፣ ለሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ አለው።
የውጪ እንግዶች የኢትዮጵያን ባሕል እና አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ፣ እንዲሁም ለሆቴሎች፣ ለአየር መንገድ እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የገቢ ምንጭ በመኾን የሀገሪቱን ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
#ሐናማርያም_መስፍን
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_13_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



