በባንክ ኦፍ አሜሪካ የቀረበው የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ዛሬ ተካሂዷል።
በውድድሩ ከ60ሺህ በላይ ሕዝብ ተሳታፊ ኾኗል። የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ዲፕሎማቶችም የውድድሩ ተሳታፊ ኾነዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ታላቁ ሩጫ በተሳታፊዎች ቁጥር እና በተቋም አደረጃጀት እያደገ መምጣቱን ጠቁሟል።
በዘንድሮው ውድድር ባንክ ኦፍ አሜሪካ የታላቁ ሩጫ አጋር በመኾኑ በፋይናንስ ረገድ ካለው እገዛ በተጨማሪ የውድድሩን ደረጃ ከፍ ማድረጉንም አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ተናግሯል።
ታላቁ ሩጫ በቀጣይ ተተኪ ትውልድ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ በመግለጽ በዘንድሮው ውድድርም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎች በባንክ ኦፍ አሜሪካ ድጋፍ ተሳታፊ መኾናቸውን ገልጿል።
የተሳታፊዎች ቁጥር በጊዜ ሂደት እያደገ መምጣቱን በማስታወስም በቀጣዮቹ ዓመታት የተሳታፊዎችን ቁጥር 70ሺህ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን ነው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ከዛሬው ውድድር በኋላ የተናገረው።
የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለስፖርት ቱሪዝም ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
በርካታ የውጭ ዜጎች እና ዲፕሎማቶች ተሳታፊ መኾናቸውን በማንሳትም ታላቁ ሩጫ ለሀገር ገጽታ እና ግንባታ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ታላላቅ ሁነቶችን በስኬት የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ለዓለም ማሳያ መድረክ መኾኑንም ጠቁመዋል።
አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት አንድ ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ሀገራችን የአትሌቶች ምድር መኾኗን ለዓለም ለማሳየትም ታላቁ ሩጫ ጉልህ አበርክቶ አለው ብለዋል።
የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ዛሬ ሲካሄድ በወንዶች ይስማው ድሉ ከአማራ ፖሊስ በሴቶች ደግሞ የኔዋ ንብረት አሸናፊ ኾነዋል።
በወንዶች ታደለ ሞሴ እና
ሮባ መርጋ 2ኛ እና 3ኛ ኾነው ጨርሰዋል።
በሴቶች አልማዝ ዮሃንስ እና አለምነሽ ጥላየ 2ኛ እና 3ኛ ኾነው አጠናቅቀዋል።
አሸናፊ አትሌቶችም 500 ሺህ፣ 200ሺህ እና 100ሺህ ብር እንደየ ደረጃቸው ከታላቁ ሩጫ ተሸልመዋል
#ባዘዘው_መኮንን
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_13_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



