“ሰባራ እግር እንጂ ሰባራ ሥነ-ምግባር አላሰለጥንም” ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ.ር)

0
78

ተስፋን ያሳየው ድል እንዳያዘናጋን እንጂ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትንሳኤ መነሻ የኾኑት ዳካረኞች በወርቆች የታጀበ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እያሳየው ያለው መዋዠቅ ጉዞውን ስጋት ውስጥ ከጣለው ከራርሟል።

መነሻ ምክንያቶቹ ከሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ባሉት ሁነቶች ላይ ሲያተኩሩ ኀላፊትን በአግባቡ አለመወጣት እና ዘመናዊ አሠራሮችን አለመከተል ትልቁን ቦታ የሚይዙ ናቸው፡፡

ለመነሻ ያክል ይሄንን ካልን ከሰሞኑ የተጠናቀው በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው የወጣቶች ኦሎምፒክን እንመልክት፡፡

በ2026 የዳካር ወጣቶች ኦሎምፒክ መድረክ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአምስት የስፖርት አይነቶች አትሌቲክስ፣ ውኃ ዋና ስፖርቶች፣ ቴኳንዶ፣ ውሹ እና ብስክሌት ውድድር በ17 ተሳታፊዎች ተካፍላለች፡፡

በአትሌቲከስ ስፖርት አምስት ወርቅ እና ሦሥት ብር ሜዳልያ በማግኘት በአጠቃላይ የዘርፉ የሜዳልያ ሰንጠረዥ አንደኛ በመኾን ማጠናቀቋ ትልቅ ተስፋን የዘራ ታሪካዊ ድል ሲኾን ስጋቶችንም ጨምሮ የመጣ ነው።

ይህ ድል ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ምንን ያመላክታል? ከዚህ በስተጀርባስ ምን ዓይነት ስጋቶች፣ ዓለም አቀፋዊ አሠራሮች እና መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ? የሚለው የዚህ ጹሑፍ ዓለማ ነው።

👉ውጤቱ እንዴት ተገኘ?

በዚህ መድረክ ትልቁ የምዕራፍ ዝግጅት የነበረው እንዲወክሉ የተመረጡት ብቻ ሳይኾኑ ተጠባባቂዎችን ጨምሮ ለበርካታ ወራት በአንድ ላይ ልምምድ እና ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ መደረጉ ትልቁ ገጽታ ነው፡፡

በወጣት አትሌቶች ዝግጅት ላይ የተደረገው ርብርብ፣ የአሠልጣኞች ጥረት እና ራሳቸውን ለአሸናፊነት ያዘጋጁት አትሌቶች የልፋት እና ጥረት ውጤት ነው።

በሜዳ ላይ ያሳዩት ብርታት፣ ጽናት እና የድል አድራጊነት መንፈስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በላቀ ኩራት ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የምንታማበትን ብቻ ሳይኾን ኾኖ የተመለከትነውን ለሰንደቅ ዓላማ መዋደቅ እንዲሁም ግለኝነትን በማስወገድ ሀገርን የማስቀደም እና የመውደድ ብስራት በጋር ለድል መብቃትን ልዑኩ ውስጥ እንዲታይ አድርጓል፡፡

👉ለኢትዮጵያ የዚህ ድል ትርጉሙ ምንድን ነው?

ከሜዳልያ ብዛት በላይ ሰፊ ነው ብለን ልንገልጸው እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማዕበሎችን አልፎ የአሁኑም ትውልድ አፍሪካዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ ብቁ መኾኑን ያረጋግጣል።

ሁለተኛ ትልቁ ተስፋ በቀጣይ ለሚመጡ የዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒኮች ጠንካራ መሠረት የሚጥል እና የቤት ሥራ የሚሰጥ፣ ለወጣቱ ትውልድም ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።

ይሄ ታዲያ የታየው ተስፋ የሚጠነክረው እነዚህን ተንከባክበን ብቻ ሳይኾን በአትሌቲክሱ ዓለም እያጋጠሙ ያሉ ሁነቶችን እንዲያልፉ በመጠበቃችን ላይ ተመስርቶ ነው፡፡

ይህም ከወረቀት ሥራዎች በተሻገረ መልኩ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሥልጣን እና ኀላፊነቱ መሠረት ከሀገርአቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር ተባብሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

👉የሚነሱት የዕድሜ ጉዳይ እና ዓለም አቀፋዊ አሠራሮች

ዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የወጣቶችን ውድድር ሲያዘጋጅ በውድድር መመሪያ እና ሕጉ ላይ በቀዳሚነት የሚያስቀምጠው የዕድሜ ገደብ ወይም የሚሳተፉት አትሌቶች ልየታ ነው፡፡

ታዲያ ከዕድሜ እርከን ውድድሮች ጋር ተያይዞ የሚነሳው የዕድሜ ጉዳይ ትልቁ ስጋት ነው። በዓለም አቀፍ አሠራር ስፖርቱ ፍትሐዊ እንዲኾን እና ወጣቶች በዕድሜያቸው ልክ እንዲወዳደሩ የዕድሜ እርከኖች ጥብቅ በኾነ መልኩ ይተዳደራሉ።

የኛ ሀገር ስጋት እና ክፍተት የመጣው ወትሮውኑም በትክክለኛ ዕድሜ አትሌቶችን መምረጥ አለመቻላችን እና በትክክለኛ ዕድሜ ቢገኙ በውጤት አያመጡም ስጋት ከውድድር ውጪ መደረጋቸው ነው፡፡

በዚህ መድረክም ከ17 ዓመት በታች ብቻ የኾኑ ተሳታፊዎች መካፈል አለባቸው ይላል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ አባት ክቡር ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ሰባራ እግር እንጂ ሰባራ ሥነ-ምግባር አላሰለጥንም በማለት በአትሌቲክሱ ዓለም ለዲሲፕሊን፣ ለሥርዓት እና ለሥነ-ምግባር የነበራቸውን የማይናወጥ ጽኑ አቋማቸውን ገልጠዋል።

ታዲያ ይሄ ከሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ የሚኖርን ሥነምግባር ብቻ አይወክልም ልኬታችን እና የሥልጠና ሂደታችንም ምን መምሰል እንዳለበት እማኝ የኾነ አመለካከታቸው ነበር፡፡

በእኛ በኩል ተገቢ ያልኾኑ አትሌቶችን ከማሰለፍ እና የዕድሜ ትክክለኛነትን ከማረጋገጥ አንጻር ሥርዓታችን አሁንም ክፍተቶች አሉት።

የዕድሜ ማጭበርበር አትሌቱ ዛሬ ከፍታ ላይ ወጥቶ እንዲሸለም ቢያደርገውም ነገ ከፍ ባሉ መድረኮች ላይ የሚጠበቀውን ቀጣይነት ሊያሳጣው እና የሀገሪቱን ገጽታ በማበላሸትም የራሱን ድርሻ እንዲወስድ ሊያደርግ ይችላል።

ይህንን ተከትሎም ሀገራችንም የራሷን ገለልተኛ የማጣሪያ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርባታል፤ የአትሌቲክስ ቁንጮ መኾናችንን መልሶ ለማግኘት ከፈለግን፡፡

ይህ ማለት ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ መውቀጥ ሳይኾን ያለአግባብ እድሉን የተጠቀሙትን እና እንዲጠቀሙ የፈቀዱትን ተጠያቂ ማድረግ ስለሚገባም ነው፡፡

ጊዜያዊ ውጤቶች መቋጫቸው ምን እንደኾነ ይታወቃልና፡፡ በዚህ በኩል ሁሉንም የስፓርት አካላት በበላይነት የሚመራው እና እንደአዲስ የተቋቋመው የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር በኩል የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል።

ለዚህ ሁሉ መድኃኒቱ ግን አሠራራችንን በማዘመን፣ ከውጪ የተቀዳ ሳይኾን ኢትየጵያን ራሷን የሚመስል የሥልጠና ሥርዓት በመዘርጋት ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የዕድሜ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ያሉትንም በበቂ ሁኔታ ማጠናከር ይገባል፡፡

👉ከዕድሜ ማጭበርበር የጸዳ ትውልድ: ለቀጣይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ዝግጅት

በአሁኑ ወቅት በአትሌቶቻችን የዕድሜ ተገቢነት ዙሪያ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ክፍተቶቻችንን አስተካክለን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማደግ ትልቅ ትምህርት ይሰጡናል።

በቀጣይ ዓመታት የሚጠብቁንን የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮናዎችን በብቃት ለመቋቋም፣ የታዳጊዎቻችን ተስፋ ሳይገድቡ በዘላቂነት ለማሻገር ሥርዓታዊ ለውጦችን ማድረግ ወሳኝ ነው።

ለዚህም ስኬት ከየትኛውም የስፖርት ፌዴሬሽን ተጽዕኖ ነፃ የኾነ፣ ዘመናዊ ሳይንሳዊ ማረጋገጫዎችን የሚጠቀም ቋሚ የዕድሜ ማጣሪያ ሥርዓት መዘርጋት ቀዳሚው ተግባር ሊኾን ይገባል።

ከዚህ ባለፈም ባሕላዊ የአሠልጣኝነት አካሄድን በመተው በስፖርት ሳይንስ፣ በሥነ-ልቦና እና በትክክለኛ የአመጋገብ ሥርዓት የታገዘ ሥልጠና በመስጠት ህልማቸው እንዳይሞት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ታዲያ አሠልጣኞችን ከማብቃት ጋር የሚያያዝም ነው፡፡

በተጨማሪም ዝምድና እና ግላዊ ጥቅማጥቅምን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ፣ በግልጽ ውድድር እና በብቃት ላይ ብቻ የተመሰረተ የአትሌቶች መረጣ ስርዓት መዘርጋት ይገባል።

እነዚህን ሥርዓታዊ ለውጦች ማካሄድ የአትሌቶችን ተስፋ እንደጉም እንዳይበተን በመታደግ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች አሸናፊ እና ኩሩ አትሌቶችን ለማፍራት ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ሊኾን ይገባል።

ሎሳንጀለስ ኦሎምፒክም ይሁን የዓለም ሻምፒዮናዎች በተከታታይ ያሉባቸው ተከታታይ ዓመታት ላይ ስንገኝ እነዚህን ታዳጊዎች ለኦሎምፒክ በብቃት ለማሸጋገር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓታዊ ለውጥ ያስፈልጋል።

👉በቀጣይ ምን ይጠበቃል?

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ሀገራት ታዳጊዎችን ይዘው ለመቆየት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ አላቸው።

ድሉ አስደሳች ቢኾንም የጉዞው የማንቂያ ደወል እንጂ ማጠቃለያ አይደለም። እነዚህ ታዳጊዎች ወደ አዋቂዎች ደረጃ ሲሸጋገሩ ተገቢው እንክብካቤ፣ አሁን ላይ አትሌቲክሳችንን እየፈተነ ያለውን የፀረ-ዶፒንግ ትምህርት፣ እንዲሁም የውድድር ዕድል እንዲያገኙ መደረግ ይኖርበታል።

በተጨማሪም የምንሳተፍባቸውን የስፖርት አይነቶች ከፍ ማድረግ ለሌሎቹ የስፖርት ዘርፎች ዕድል መስጠት እና ማዘጋጀት ደግሞ ከጎረቤቶቻችን የምንወስደው ልምድ ነው።

ታዲያ ተስፋን ያሳየው ድል ወጣቶቻችን ላይ መሥራታችንን ከቀጠልን የነገ አበበ፣ ፋጡማ፣ ደራርቱ ፣ኃይሌ ፣ጥሩነሽ፣ ስለሺ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት፣ ለተሰንበት፣ ታምራት እና መሰል የሀገራችን እንቁዎች መኾናቸው አይቀርም፡፡

የ2028 ሎስአንጀለስ ኦሎምፒክ ቅርብ ነው!

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም

በሐናማርያም መሥፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here