በዳካር የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ተሳተፊ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ አዲስ አበባ የገባ ሲኾን በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቀባበል ተደርጎለታል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) የዳከር ወጣቶች ኦሎምፒክ አዲስ ተስፋ የሰነቅንበት እና አዲስ ድል ያስመዘገብንበት ትልቅ መድረክ ነበር ብለዋል።
የ2028ቱ የሎሳንጀለስ ኦሎምፒክ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ እንደቀረው ያስታወሱት ዶክተር አሸብር በተከታታይ ዓመታት በኦሎምፒክ የጠፋውን ውጤት ለመመለስ እነዚህ ወጣት አትሌቶች ሳይበተኑ ካሁኑ ዝግጅት መጀመር እንዳለበት ገልጸዋል።
በአትሌቲክሱ ያለንን ታሪካዊ ውጤት እና ድል ለማስቀጠል በአንድነት እና በትብብር መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአትሌቶች ምድር መኾኗን የገለጹት የኢፌዴሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ.ር) የቀድሞውን የአሸናፊነት ታሪክ የሚያስቀጥሉ ተተኪ ወጣቶች ዳካር ላይ መታየታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ስፖርትን ከውድድር ባለፈ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት፣ ልማት እና ዲፕሎማሲ አንዱ መሠረት እንዲኾን ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ዶክተር አክሊሉ ተናገረዋል።
ለዚህም ለስፖርት መሠረተ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በወጣቶች ኦሎምፒክ የተገኘውን ድል እንደ ስንቅ በመጠቀም በቀጣይ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤታማ ለመኾን መሥራት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በቀጣይ ለሚደረጉት የዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ መድረኮች ከአሁኑ ዝግጅት እንደሚጀመርም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በወጣቶች ኦሎምፒክ የተገኘው ውጤት እንዲቀጥል የተጠናከረ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቲክስ ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የልዑኩ ቡድን መሪ ገዛኸኝ ወልዴ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት ከስድስት ወራት በላይ ያደረገው ዝግጅት እና ክትትል ለውጤቱ ዋና መሠረት ነበር።
በኬኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአኖካ ዞን አምስት ወጣቶች ጨዋታ መሳተፋችን አትሌቶች የውድድር ልምድ እንዲያገኙ እና ዳካር ላይ ስኬታማ እንዲኾኑ አድርጓልም ብለዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች ቴዎድሮስ ኃይሉ እና ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ የነበረው የተደራጀ ዝግጅት፣ ክትትል እና ድጋፍ ለውጤት እንዳበቃቸው በመግለጽ አትሌቶቻችን በሴኔጋል ዳጋር የነበረውን ከፍተኛ ሙቀት በመቋቋም ሀገርን ያኮራ ድል አስመዝግበዋል ብለዋል።
ይህ ውጤት ጅምር እና ለነገ ስንቅ መኾኑን የገለጹት አትሌቶች በበኩላቸው ተግተው በመሥራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ ማድረግን እንደሚያልሙ ገልጸዋል።
በዳካር ወጣቶች ኦሎምፒክ በአምስት የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክስ አምስት ወርቅ እና ሦሥት ብር በማግኘት ከአለም 1ኛ ኾና ማጠናቀቋ ይታወሳል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
በባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



