“‎የዳካር ወጣቶች ኦሎምፒክ አዲስ ተስፋ እና አዲስ ድል የተመዘገበበት ነው” አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር)

0
61

‎በዳካር የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ተሳተፊ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ አዲስ አበባ የገባ ሲኾን በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቀባበል ተደርጎለታል።
‎
‎የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) የዳከር ወጣቶች ኦሎምፒክ አዲስ ተስፋ የሰነቅንበት እና አዲስ ድል ያስመዘገብንበት ትልቅ መድረክ ነበር ብለዋል።
‎
የ‎2028ቱ የሎሳንጀለስ ኦሎምፒክ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ እንደቀረው ያስታወሱት ዶክተር አሸብር በተከታታይ ዓመታት በኦሎምፒክ የጠፋውን ውጤት ለመመለስ እነዚህ ወጣት አትሌቶች ሳይበተኑ ካሁኑ ዝግጅት መጀመር እንዳለበት ገልጸዋል።
‎
‎በአትሌቲክሱ ያለንን ታሪካዊ ውጤት እና ድል ለማስቀጠል በአንድነት እና በትብብር መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
‎
‎ኢትዮጵያ የአትሌቶች ምድር መኾኗን የገለጹት የኢፌዴሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ.ር) የቀድሞውን የአሸናፊነት ታሪክ የሚያስቀጥሉ ተተኪ ወጣቶች ዳካር ላይ መታየታቸውን ገልጸዋል።
‎
‎መንግሥት ስፖርትን ከውድድር ባለፈ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት፣ ልማት እና ዲፕሎማሲ አንዱ መሠረት እንዲኾን ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ዶክተር አክሊሉ ተናገረዋል።
‎
‎ለዚህም ለስፖርት መሠረተ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
‎
‎በወጣቶች ኦሎምፒክ የተገኘውን ድል እንደ ስንቅ በመጠቀም በቀጣይ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤታማ ለመኾን መሥራት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
‎
‎በቀጣይ ለሚደረጉት የዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ መድረኮች ከአሁኑ ዝግጅት እንደሚጀመርም አመላክተዋል።
‎
‎የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በወጣቶች ኦሎምፒክ የተገኘው ውጤት እንዲቀጥል የተጠናከረ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎
‎እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቲክስ ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
‎
‎የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የልዑኩ ቡድን መሪ ገዛኸኝ ወልዴ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት ከስድስት ወራት በላይ ያደረገው ዝግጅት እና ክትትል ለውጤቱ ዋና መሠረት ነበር።
‎
‎በኬኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአኖካ ዞን አምስት ወጣቶች ጨዋታ መሳተፋችን አትሌቶች የውድድር ልምድ እንዲያገኙ እና ዳካር ላይ ስኬታማ እንዲኾኑ አድርጓልም ብለዋል።
‎
‎የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች ቴዎድሮስ ኃይሉ እና ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ የነበረው የተደራጀ ዝግጅት፣ ክትትል እና ድጋፍ ለውጤት እንዳበቃቸው በመግለጽ አትሌቶቻችን በሴኔጋል ዳጋር የነበረውን ከፍተኛ ሙቀት በመቋቋም ሀገርን ያኮራ ድል አስመዝግበዋል ብለዋል።
‎
‎ይህ ውጤት ጅምር እና ለነገ ስንቅ መኾኑን የገለጹት አትሌቶች በበኩላቸው ተግተው በመሥራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ ማድረግን እንደሚያልሙ ገልጸዋል።
‎
‎በዳካር ወጣቶች ኦሎምፒክ በአምስት የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክስ አምስት ወርቅ እና ሦሥት ብር በማግኘት ከአለም 1ኛ ኾና ማጠናቀቋ ይታወሳል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም

በባዘዘው መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here