ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወጣቶች ኦሎምፒክ

0
103

 

በፈረንጆቹ 2010 በሲንጋፖር መካሄድ የጀመረው የአለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ከቀናት በኋላ 4ተኛ መድረኩን በዳካር ያስተናግዳል፡፡

በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የማከናወን ሀላፊነቱን የተቀበለችው ምእራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል ዳካር ላይ ከጥቅምት 21 እስከ ህዳር 4 ድረስ ይከናወናል፡፡ ከ206 ሀገራት የተወጣጡ ከ2700 በላይ አትሌቶች በተለያዩ ስፓርታዊ ውድድሮች ለሀገር ክብርና ለሜዳልያ ይፋለማሉ፡፡

ኢትዮጰያም ከ1 ሳምንት በኋላ በሚደረገው በዚህ መድረክ በአትሌቲክስ ፣በውሃ ዋና፣ በቴኳንዶ፣ በውሹና በብስክሌት ስፖርቶች ትካፈላለች፡፡ ወጣቶቹ መጻኢ እድላቸውን የሚያዩበትና ከአለምአቀፉ መድረክ ጋር የሚተዋወቁበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ሶስት መድረኮች የነበራት ውጤት ስንመከከት፡-

ሲንጋፖር እ.ኤ.አ 2010 – በአትሌቲክስና በውሃ ዋና

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የወጣቶች ኦሎምፒክ ተሳትፎዋ 7 ልኡካንን የያዘ ቡድን ስትልክ 5 ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ አጠናቃለች፡፡

ሞሀመድ አማን፣ ፍቅሩ ጀቤሳ፣ ሐብታሙ ጃለታ፣ ትዝታ ቦጋለ፣ ጸሀይነሽ ጸንጋ በአትሌቲክስ እንዲሁም ሮቤል ኪሮስና ያኔት ስዩም ደግሞ በውሃ ዋና ስፖርት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በመድረኩ ሀገራችን 2 ወርቅና 3 ነሀስ ሜዳልያዎችን በአትሌቲክስ አምጥታለች፡፡ ሞሀመድ አማን በወንድ 1000 ሜትርና በሴት ትዝታ ቦጋለ በተመሳሳይ በ1000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ለሀገራቸው ሲያስገኙ በ3000 ሜትር ወንድ ፍቅሩ ጀቤሳ፣ሐብታሙ ጃለታ በ2000 ሜትር መሰናክል እና በ2000 ሜትር ሴቶች ጸሀይነሽ ጸንጋ የብር ሜዳልያ አምጥተዋል፡፡

ናንጂንግ ቻይና እ.ኤ.አ 2014

ከ3580 በላይ ተሳታፊዎች በደመቁት በዚህ መድረክ ሀገራችንም በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ በ15 ተሳታፊዎች 8 ሜዳልያዎችን ያመጣችበት ነው፡፡

አሁን ላይ ለክብረወሰን ሰአቶች ከመጠበቁ ባለፈ በየርቀቶቹ ከሰአት ጋር ፍጥጫ ላይ ያለው ዮሚፍ ቀጀልቻ የተዋወቀውም በዚህ መድረክ ነው፡፡

ኢትዮጰያ 8 ሜዳልያዎችን ስታገኝ 3 ወርቅ 2 ብርና 3 ነሃስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ በነዚህም ቻይናን በመከተል ከአለም 2ተኛ ሆነን ያጠናቀቅንበት መድረክም ሆኖ አልፏል፡፡

በወንዶች 3000 ሜትር ዮሚፍ ቀጀልቻ 7 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ከ20 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ሆኖ በመድረኩ ወርቅ በማጥለቅ የታሪክ ተጋሪ ሆኗል፡፡ ወገኔ ሰብስቤ በ2000 ሜትር ፣ኮከብ ተስፋይ በሴቶች 1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያዎችን ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡

ሀዊ አለሙ በ800 ሜትር ሴቶች፣ሙሉጌታ አሰፋ በወንዶች 1500 ሜትር፣ ዘውድነሽ ማሞ በ2000 ሜትር መሰናክል እንዲሁም ቤዛ ዘገየ በድብልቅ በወንዶች 8 በ100 ሜትር የዱላ ቅብብል የብር ሜዳልያዎች ባለቤት ሆነዋል፡፡

በ3000 ሜትር ሴቶች ብርሃን ደሚሳ ፣ባጫ ሞርካ እንዲሁም ሙሉጌታ አሰፋ በድብልቅ 8 በ100 ሜትር ዱላ ቅብብል 3ተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳልያን ገቢ አድርገዋል፡፡

2018 እ.ኤ.አ ቦነስ አይረስ አርጀንቲና

በብስክሌት ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣቶች ኦሎምፒክ በተሳተፍንበት ወጣቶች ኦሎምፒክ ሜዳልያዎቹ የተገኙትበአትሌቲክስ ብቻ ነው፡፡ በ8 ሜዳልያዎች 33 ደረጃን ቦነስ አይረስ ስናጠናቅቅ 2 ወርቅ፣ 2 ብርና 4 ነሀስ ተመዝግበዋል፡፡

በአትሌቲክስ 9 በብስክሌት ደግሞ 2 ብስክሌተኞችን ባሳተፍንበት የ2018 መድረኩ እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ በአትሌቲክሱ ደማቅ ውጤት ተመዝግቧል። አብርሃም ስሜ ወርቅና መለሰ ንብረት ነሀስ ሜዳልያን ካስመዘገቡት መካከልም ናቸው፡፡

አብርሃም ስሜ በ2,000 ሜትር መሰናክል እና ጣሰው ያዳ በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው አስገኝተዋል። መቅደስ አበበ በሴቶች 2000 ሜትር መሰናክል፣በሪሁ አረጋዊ በወንዶች 3000 ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን አሳክተዋል። ሂሩት መሸሻ በሴቶች 800 ሜትር፣ ለምለም ኃይሉ በሴቶች 1500 ሜትር፣ አበራሽ ምንሴዎ በሴቶች 3000 ሜትር እና መለሰ ንብረት ደግሞ በወንዶች 1500 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ ማግኘት ችለዋል።

በብስክሌት ስፖርት ዘርፍ ታዳጊዎቹ ዛይድ ኃይሉ እና ጻድቃን ካሳሁን በቡድን ውድድር ላይ በመሳተፍ ጥሩ ተሞክሮ አግኝተው የተመለሱበትም ነበር። ኢትዮጵያ በድምሩ በ2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 4 ነሐስ ውድድሩን ከአለም 33ኛ ደረጃ አጠናቃለች።

የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ አበርክቶ ያደረጉ መድረኮች መሆናቸው የመካድ ሀቅ አይደለም፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ታሪካቸውን የጀመሩት እንደ መሀመድ አማን፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ በሪሁ አረጋዊ እና መቅደስ አበበ፣ሂሩት መሸሻና መለሰ ንብረት ያሉ አትሌቶች ከዓመታት በኋላ በየዓለም ሻምፒዮና እና በዋናው የኦሎምፒክ መድረክ ላይ ለሀገራቸው ትልልቅ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ ዳካር ላይ በ5 የስፖርት አይነት 18 ተሳታፊዎቻቸው ቀጣዩን የስኬት ጉዟቸውን የሚጽፉበትን ውድድር ያደርጋሉ፡፡ መልካም እድል እንዲገጥማቸው እንመኛለን፡፡

ሐናማርያም መስፍን

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_16_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here