የኬፕ ቨርዴው ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ቮዚኛ ለዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ለሚሰጠው ታዋቂው የያሺን ትሮፊ እጩ ኾኖ በመመረጡ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጿል።
ተጫዋቹ ስለ እጩነቱ በሰጠው አስተያየት መረጃውን በሰማበት ወቅት ነገሩ ቀልድ መስሎት እንደነበር በመግለጽ “ብዙዎች እጩነቴ ተገቢ አይደለም ሊሉ ይችላሉ፤ በከፊል እኔም ቢኾን ተመሳሳይ ስሜት ይሰማኛል” ብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልልቅ ሊጎች ለሚጫወቱ ታላላቅ ግብ ጠባቂዎች ትልቅ አክብሮት እንዳለው የጠቆመው ቮዚኛ በዕድሜው እና በሙያ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ይህን ክብር ማግኘቱ የተሰጠው ትልቅ ስጦታ መኾኑን በመጥቀስ ለመረጡት አካላት ምሥጋናውን አቅርቧል።
በታዋቂው የፈረንሳይ የስፖርት መጽሔት “ፍራንስ ፉትቦል” አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚሰጠው የያሺን ትሮፊ ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ግብ ጠባቂዎች የሚሰጥ ታላቅ ክብር ሲኾን ሽልማቱም በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው ታላቁ የባሎንዶር የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ወቅት ለአሸናፊው የሚበረከት ይኾናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



