“በኮፐንሀገን የተመዘገበው ውጤት የሀገራችንን አትሌቲክስ እውነተኛ ገጽታ ያሳየ ነው” ኢንስትራክተር መሠረት መንግሥቱ

0
85

 

በዴንማርክ ኮፐንሀገር ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ4 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቃለች።

በውድድሩ 13 ሀገራት በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መካተት የቻሉ ሲኾን ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኬንያ በመቀጠል ነው ውድድሩን ያጠናቀቀችው።

የተመዘገበውን ውጤት አስመልከተው አስተያየታቸውን የሰጡት ኢንስትራክተር አሠልጣኝ መሠረት መንግሥቱ ውድድሩ የሀገራችን አትሌቲክስ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ትክክለኛ ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ብለዋል።

ኢንስትራክተር አሠልጣኝ መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ በቂ የዝግጅት ጊዜ ሳይኖረው ለውድድር የተጓዘ እንደኾነ እና የተገኙት ሜዳሊያዎችም በዋናነት በአትሌቶቹ የግል ብቃት እና ጥረት ብቻ እንደኾነ ጠቅሰዋል።

በዝግጅት ወቅት አብረዋቸው የነበሩ አሠልጣኞች ያሠለጠኗቸውን አትሌቶች በውድድሩ ወቅት መምራት ያልቻሉበት አጋጣሚ ተፈጥሯልም ነው ያሉት።

በውድድሩ የወንድ አትሌቶች ውጤት የራቃቸው ሲኾን ሴት አትሌቶች በቁጥር አነስተኛ ቢኾኑም አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ሀገርን አኩርተዋል ብለዋል።

በሀገራችን አትሌቲክስ ላይ የሚታየው ችግር እየበረታ መምጣቱን የጠቆሙት ኢንስትራክተር መሠረት፣ በተለይም በወንዶች አትሌቲክስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም አሁንም ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት አለመፈለጉ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው አሳስበዋል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

በዳናይት ሲሳይ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here