የፕሪምየር ሊጉ ወደ ባሕር ዳር መመለስ ለስፖርቱ አዲስ የብሩህ ተስፋ ጭላንጭል ያሳያል” አቶ ክፍሌ ሰይፈ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2019 የውድድር ዓመት የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ሲያከናውን፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከ30 በላይ የሊግ ጨዋታዎች የሚካሄዱበት ዋና መድረክ ኾኖ ተመርጧል። በቅርቡ በካፍ ሙሉ ዕውቅና ያገኘው ይህ ዘመናዊ ስታዲየም፣ የባሕር ዳር ከተማ እና የፋሲል ከነማ ክለቦች ዋና መጫወቻ ሜዳ ኾኖ የሚያገለግል ሲኾን፣ ሁለቱ ክለቦች 34 የሜዳቸውን ጨዋታዎች በዚሁ ስታዲየም ያከናውናሉ። ይህም የሊጉ ጨዋታዎች ከ2015 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውቧ ጣና ዳርቻ ከተማ የመመለሳቸውን ታሪካዊ ማረጋገጫ የሰጠ ነው።
ቋንቋ፣ ባሕል እና ብሔር ሳይገድብ በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችን በአንድ ላይ የሚያገናኝ ውብ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እንደኾነ የሚገለጸው እግር ኳስ፣ ከውጤት እና ከሦሥት ነጥብ በላይ የኾነ የማኅበረሰብ ስሜት፣ ፍቅርና ኅብረት መግለጫ ነው። ላለፉት አምስት ዓመታት የሞቀ የደጋፊዎችን ሆታ ሳያስተናግድ፣ ከጣና ሐይቅ በሚነሳው ነፋሻማ አየር አጅቦ እልልታ ሳይሰማበት ጸጥ ብሎ የቆየው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ አሁን ግን ያ ረጅም የጥበቃ እና የናፍቆት ጊዜ ሊያበቃ እና የደስታ ምዕራፍ ሊከፈት ተዘጋጅቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ ክፍሌ ሰይፈ የሊጉ ጨዋታዎች ወደ ባሕር ዳር መመለሳቸውን አስመልክተው ለአሚኮ ስፖርት በሰጡት አስተያየት፣ የስፖርቱ መመለስ ለሀገር ውስጥ እግር ኳስ አዲስ የብሩህ ተስፋ ጭላንጭል የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል። አቶ ክፍሌ አክለውም «እግር ኳስ ከፖለቲካና ከሃይማኖት ልዩነቶች የጸዳ፣ ተጫዋቾች በክህሎት እና በስፖርታዊ ጨዋነት የሚዝናኑበት ትልቅ መድረክ ነው» ብለዋል።
ስታዲየሙ በካፍ የመመዘኛ መስፈርት መሠረት የተገነባ፣ ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ደጋፊዎችን የመያዝ አቅም ያለው እና ለቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲሁም ለጋዜጠኞች የሥራ ሂደት ምቹ መኾኑን የጠቆሙት ሥራ አሥፈጻሚው፤ በቅርብ ሳምንት የሚደረገውን የአማራ ደርቢ ጨምሮ ሌሎች መርሐ-ግብሮች በናፈቀው ማኅበረሰብ ዘንድ በደማቅ ሁኔታ እንደሚስተናገዱ አብራርተዋል። ቀደም ሲልም ስታዲየሙ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ውጭ በነበሩ የክለቦች መርሐ-ግብር በአንድ ጨዋታ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ደጋፊዎችን ያስተናገደበት አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል።
የጨዋታዎች ወደ ባሕር ዳር ከተማ መመለስ በሜዳ ውስጥ በሚደረገው 90 ደቂቃ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። በቅርብ ጊዜያት በኮሪደር ልማት በከፍተኛ ሁኔታ የተዋበችው እና አዳዲስ ዘመናዊ ሆቴሎችን እያስገነባች ያለችው ባሕር ዳር፣ ከስፖርቱ የሚገኘውን ያልተነካ የስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ዝግጅቷን አጠናቃለች። ከመላው ሀገሪቱ የሚመጡ ክለቦች፣ ጋዜጠኞች እና ደጋፊዎች ለከተማዋ የንግድ፣ የሆቴል እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አዲስ ሕይወት የሚዘሩ ይኾናል።
አቶ ክፍሌ የስፖርቱን የኢኮኖሚ አቅም ከማዕድን ሀብት ጋር በማወዳደር ሲያስረዱ «የከተሞች የስፖርት ኢንዱስትሪ በአንድ ጨዋታ ከ4 እስከ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ የማስገኘት አቅም ያለው በመኾኑ፣ ከነዳጅ እና ወርቅ ማዕድን ያልተናነሰ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ተደርጎ ሊታሰብ ይገባል» ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የስፖርት አፍቃሪው ከረጅም አምስት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ ተወደደው ስታዲየም የሚመልሰው የደስታ እና የድጋፍ ድምጽ፣ የጣና ዳሯን ከተማ ዳግም በስፖርት ፍቅር፣ በሰላም እና በወንድማማችነት የሚያደምቃት አዲስ ብሩህ ምዕራፍ እንደሚኾን ይጠበቃል። ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ በሚደረገው ደማቅ መርሐ-ግብር ላይ የብዙዎች ዐይን ያርፋል።
#አሚኮ #ኢትዮጵያ_ፕሪሚየር_ሊግ #ባሕር_ዳር #ፋሲል_ከነማ #ባሕር_ዳር_ከተማ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_08_2019_ዓ_ም
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



