በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ እና የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ፣ ቡድናቸው ለ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
አሠልጣኙ አክለውም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ከሚገኙ 18 ክለቦች መካከል 16ቱ የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን የሚጠቀሙ መኾናቸውን ገልጸው ይህም ሀገሪቱ ከፍተኛ የግብ ጠባቂ እጥረት እንዳጋጠማት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ይህንን ስጋት ለመቅረፍ እና ወጣት ግብ ጠባቂዎችን ለማፍራት ክለቦች ተባብረው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱበት ዕድል ሊመቻች እንደሚገባ አሠልጣኝ ዮሃንስ አሳስበዋል።
በአውሮፓ እና በአሜሪካ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሊጎች የሚጫወቱ ከ40 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እንዲሁም ከ17 እና ከ19 ዓመት በታች ያሉ ከ60 በላይ ታዳጊዎች ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች እንዳሏቸው ጠቁመዋል።
ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ያሉትን እንቅፋቶች በመፍታት የእነዚህን ተጫዋቾች አቅም መጠቀም እንደሚገባም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጅራ በበኩላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ለሀገራቸው መጫወት የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ከሕግ እና ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እና ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



