የፍራንክ ላምፓርድ አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ፈተና።

0
98
ከ25 ዓመታት በኋላ ኮቨንተሪ ሲቲን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገው ሰው አሁን ግን ያንኑ ቡድን በከፍተኛው የእንግሊዝ ሊግ ማቆየት ይችላል ወይ የሚለው ጉዳይ የፍራንክ ላምፓርድ አዲሱ ፈተና ኾኗል።
ከቼልሲ የምንጊዜም ባለውለታ እና ጀግኖች መካከል አንዱ የኾነው ፍራንክ ላምፓርድ ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝነት ከተሸጋገረ በኋላ በቼልሲ እና ኤቨርተን የተለያዩ ፈተናዎችን አሳልፏል።
ነገር ግን በኮቨንተሪ የሠራው ሥራ ለአሠልጣኝነት ጉዞው አዲስ ተስፋ ፈጥሯል። ላምፓርድ ኮቨንተሪን በችግር ውስጥ እያለ ተረክቦ በትዕግስት እና በተግባራዊ አሠልጣኝነት ቡድኑን ከፍ አድርጎታል።
በ2025/26 የሻምፒዮን ሺፕ ዘመን ላምፓርድ የሚመራው ኮቨንተሪ አስደናቂ የኾነ ዘመን ያሳለፈ ሲኾን ቡድኑ የሻምፒዮን ሺፑ ሻምፒዮን በመኾን ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ተመልሷል።
ለኮቨንተሪ ይህ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ነበር። ለላምፓርድ ደግሞ እንደ አሠልጣኝ ብቃቱን እንደገና የሚያሳይበት ታላቅ ዕድል ፈጥሮለታል።
ክለቡም በእሱ ሥራ በመተማመን ውሉን እስከ 2029 አራዝሞለታል። ነገር ግን ፕሪምየር ሊጉ በተለየ ፈተና ነው የተቀበለው።
ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተመለሰ በኋላ ጅማሬው እጅግ አስቸጋሪ የኾነበት ኮቨንትሪ ገና ከወዲሁ በ4 ተከታታይ ሽንፈቶች ውስጥ ይገኛል። በተለይም በብራይተን የደረሰበት የ5 ለ 0 ሰፊ ሽንፈት በላምፓርድ እና በቡድኑ ላይ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።
እናም አሁን ዋናው ጥያቄ ላምፓርድ በሻምፒዮን ሺፕ ያሳየውን ስኬት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማምጣት ቡድኑን ማቆየት ይችላል ወይ? የሚለው ኾኗል።
ፕሪሚየር ሊጉ ጥልቅ እና ጥራት ያለው የተጫዋቾች ሥብሥብ፣ የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ፍጥነትን በአግባቡ መቆጣጠር እንዲሁም በጠንካራ ተጋጣሚዎች ላይ ሳይቀር ነጥብ መሠብሠብን ይጠይቃል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ላምፓርድ እነዚህን ነገሮች ለማሳካት አሁን ለሁለት ጉዳዮች መፍትሄ ማግኘት አለበት። አንደኛው ቡድኑ እየታየበት ያለውን በርካታ ግቦች የማስተናገድ ችግር ለመቅረፍ የመከላከል መዋቅሩን ማጠናከር ሁለተኛው ደግሞ በተጋጣሚው የግብ ክልል ውስጥ የበለጠ ውጤታማ መኾን ነው።
ኾኖም አሁን ባለው ሁኔታ ኮቨንተሪ ከታላላቅ ክለቦች ጋር ሲነፃፀር የተጫዋቾች ጥራት እና የገንዘብ አቅም ልዩነት በግልጽ እየታየበት ይገኛል።
ከሻምፒዮን ሺፕ ሻምፒዮንነት ወደ ፕሪምየር ሊግ መድረክ መድረስ አንድ ነገር ነው፤ በዚያ ታላቅ መድረክ መቆየት ግን ፍጹም የተለየ ፈተና ነው።
እናም ይህንን ፈተና ተወጥቶ ኮቨንተሪን እንደገና ማንሳት ይችላል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ለፍራንክ ላምፓርድ በአሠልጣኝነት ሕይወቱ እጅግ ወሳኝ ሊኾኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በዳናይት ሲሳይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here