በ400 ሜትር መሰናክል ሩጫ ለዓመታት በርካታ ድሎችን በመቀዳጀት የስፖርቱን የከፍታ ዘመን የመራችው አሜሪካዊቷ አትሌት ዳሊላህ ሙሐመድ ከስፖርቱ ዓለም በይፋ መሰናበቷን አስታውቃለች።
አትሌቷ በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ አልቲሜት ሻምፒዮንሺፕ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ በመወዳደር የስፖርት ዘመኗን አጠናቅቃለች።
ከውድድሩ አስቀድሞ ለኤንቢሲ ጋዜጠኛ ሌዊስ ጆንሰን በሰጠችው አስተያየት፣ ውድድሩ የመጨረሻዋ መኾኑን የገለጸችው ዳሊላህ በፍጻሜው ውድድር 53 ሰከንድ ከ11 ማይክሮሰከንድ በመግባት የዓመቱ ፈጣን ሰዓቷን አሻሽላ 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቃለች።
በዚህም የ25 ሺህ አሜሪካን ዶላር ተሸላሚ ኾናለች። የ36 ዓመቷ ዳሊላህ ሙሐመድ በ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በ400 ሜትር መሰናክል፣ በ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ በ4×400 ሜትር ዱላ ቅብብል እንዲሁም በ2019 የዶሃ ዓለም ሻምፒዮና በሁለቱም ርቀቶች የወርቅ ሜዳልያዎችን በመቀዳጀት በውድድር መድረኮች የበላይነቷን አረጋግጣ ነበር።
በተጨማሪም የ400 ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ ወሰንን ሁለት ጊዜ መስበር የቻለች ሲኾን፣ በዶሃ ያስመዘገበችው 52 ሰከንድ ከ16 ማይክሮሰከንድ ሰዓት የርቀቱን ታሪክ የቀየረ ነበር።
በዋና ዋና ዓለም አቀፍ መድረኮች 13 ሜዳልያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 25 ጊዜ በሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገባችው አትሌቷ 10 የዲያመንድ ሊግ ዋንጫዎችንም ተቀዳጅታለች።
ዳሊላህ ሙሐመድ ያጋጠሟትን ተደጋጋሚ ጉዳቶች እና የነበረውን ከፍተኛ ፉክክር በጽናት በመቋቋም ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ አርዓያ መኾኗ ተገልጿል።
ከውድድር ሜዳ ብትረቅም ከአትሌቲክስ ስፖርት ሳትለይ የቀጣዩን ትውልድ ዕድገት በደጋፊነት ለመከታተል ፍላጎት እንዳላትም አስታውቃለች።
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



