ታንዛኒያዊቷ ክላራ ሉቫንጋ በ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የሴቶች እግር ኳስ ውድ ተጫዋች ኾናለች። የ21 ዓመቷ ታንዛኒያዊት አጥቂ ክላራ ሉቫንጋ ከሳዑዲው አል ናስር ወደ አሜሪካው ዋሺንግተን ስፒሪት በ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በመዛወር በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ውዷ ተጫዋች ኾናለች።
ይህ ዝውውር በሲዊድናዊቷ ፌሊሺያ ሺሮደር ተይዞ የነበረውን የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሴቶች የዝውውር ክብረወሰን የሰበረ ነው።
ከሳዑዲ አረቢያው ክለብ ጋር ባለፉት ሦሥት ዓመታት የሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችላለች።
በአንድ የውድድር ዓመትም 24 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመባል ዘውዱን ደፍታለች። ባለፈው የውድድር ዘመን ለአል ናስር ሴቶች ክለብ በ23 ጨዋታዎች 33 ግቦችን ያስቆጠረችው ሉቫንጋ ከአሜሪካው ክለብ ጋር እስከ 2029 የሚያቆያትን የ4 ዓመት ውል ተፈራርማለች።
“ህልሜ እውን ኾኗል” ስትል የተናገረችው ሉቫንጋ “ታንዛኒያን እና አፍሪካን ኩሩ ማድረግ እፈልጋለሁ” ብላለች። በአሁኑ ሰዓት በNWSL የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ዋሺንግተን ስፒሪትን የተቀላቀለችው ሉቫንጋ፣ ከክለቡ ድንቅ አጥቂ ትሪኒቲ ሮድማን ጋር በመጣመርም ለቡዱኑ የላቀ ግልጋሎት ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል ሲል ዋሽንግተን ፓስት ዘግቧል።
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



