የማይረሱ የአውሮፖ ቻምፒዮንስ ሊግ ክስተቶች ትውስታ፡፡

0
131
የ2026/27 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ምሽት በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
የዘንድሮው ውድድር ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በቻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ ውስጥ ከማይረሱ ክስተቶች መካከል ሦሥቱን ወደኋላ መለስ ብለን እናስታውስ።
በቀዳሚነት የኢስታንቡሉ የሚጠቀስ ሲኾን በፈረንጆቹ 2005 ሊቨርፑል ከኤሲ ሚላን ለፍጻሜ የተገናኙበት ነበር፡፡
በጨዋታው እስከ እረፍት ድረስ 3 ለ 0 እየተመራ የነበረው ሊቨርፑል ውጤቱን ይቀለብሳል ያለ ብዙም አልነበረም።
ኾኖም በሁለተኛው አጋማሽ አስገራሚ በኾነው ትዕይንት ሊቨርፑል በ6 ደቂቃዎች ውስጥ 3 ግቦችን አስቆጥሮ አቻ በመኾን በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት አሸንፎ ዋንጫውን ያነሳበት ክስተት እስከዛሬ የቻምፒዮንስ ሊጉ ታላቁ ተአምር ተብሎ ይታወሳል።
የማንችስተር ዩናይትድ የ1999 የባከነ ሰዓት ድል እና ሻምፒዮናነት ሌላው አሁንም ድረስ የሚታወስ ክስተት ነው።
በወቅቱ በማንችስተር ዩናይትድ እና በባየር ሙኒክ መካከል በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ዩናይትድ እስከ 90ኛው ደቂቃ 1ለ0 እየተመራ በባከኑ 3 ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2 ለ 1 አሸንፎ ዋንጫውን የወሰደበት አጋጣሚ በክለቡ ታሪክ በወርቅ ቀለም ተጽፏል፤ በቻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክም ከማይረሱ ክስተቶች አንዱ ኾኗል፡፡
ሌላው የማይረሳው ክስተት በ2002ቱ ውድድር የዚነዲን ዚዳን አስደናቂ ግብ ነው፡፡
በወቅቱ ለሪያል ማድሪድ ይጫወት የነበረው ፈረንሳዊው ኮከብ ዚነዲን ዚዳን ባየር ሌቨርኩሰን ላይ ከአየር ላይ ሳይወርድ በግራ እግሩ ያስቆጠራት ግብ በቻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ አስደናቂዋ ግብ ተብላ ትታወሳለች።
በዳናይት ሲሳይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here