በድንቅ ብቃቱ ደጋፊውን እያሳመነ የመጣው ዝምተኛው ገዳይ።

0
130

 

ክህሎቱን ጠንቅቀው በሚረዱት እና ለፍልስፍናቸው ተስማሚ መኾኑን በሚያውቁት አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቀዳሚ ተመራጭ ተጫዋች ነው ጀርመናዊው ካይ ሃቨርትዝ።

በሜዳ ውስጥ በሚያሳየው ረቂቅ ጥበብ እና ልዩ አጫወት የዘመናዊ እግር ኳስን ውበት በግልጽ የሚያንጸባርቅ ልዩ ተጫዋች መኾኑን እያሳየ ይገኛል።

ሃቨርትዝ በሜዳ ላይ ከሚያሳያቸው አስደናቂ እንቅስቃሴዎች መካከል የተጋጣሚ ተከላካዮች ባልተገነዘቡት ቅጽበት ባዶ ቦታዎችን የመፈለግ እና የመጠቀም ችሎታው ነው።

ከኳስ ውጭ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ውጥረት ውስጥ የሚክቱ እና ለቡድን አጋሮቹ ሰፊ የማጥቃት ዕድል የሚከፍቱ ናቸው።

በተጣበበ እና ውጥረት በበዛባቸው የጨዋታ አጋጣሚዎች ላይ የሚያሳየው የተረጋጋ ስሜት እና ውሳኔ አሰጣጥም አስደናቂ ነው።

ኳስን ከመረብ ማሳረፍ ብቻ ሳይኾን ተከላካዮችን በሀሰተኛ እንቅስቃሴዎች በማታለል ለቡድን አጋሮቹ ግብ የማስቆጠሪያ ዕድል የመፍጠር ብልሃቱ የእግር ኳስ አዕምሮው ምን ያህል የሰላ እንደኾነ ያሳያል።

9 ቁጥር አጥቂ ኾኖ በአየር ላይ ኳሶች ተከላካዮችን መፈተን የሚችል እና በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍጎ እንደ ቁጥር 10 አጫዋች ቡድን ማያያዝን የሚያውቅ ብልህ ነው።

ይህ ሁለገብነቱም የአሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ የታክቲክ መፍትሄ ሲያደርገው ለተጋጣሚ ቡድን ደግሞ ለመያዝ አስቸጋሪ የኾነ እንቆቅልሽ እንዲኾን አስችሎታል።

ካይ ሃቨርትዝ በደጋፊዎች ዘንድ ብዙም የሚዘመርለት ተጫዋች አይደለም።

ይሁን እና ጨዋታን በቀላል እና ማራኪ መንገድ የመምራት፣ የቡድኑን ማጥቃት የማቀላጠፍ እና በወሳኝ ቅጽበቶች ጨዋታን የመቀየር ልዩ ተፈጥሯዊ ስጦታ ያለው ተጫዋች መኾኑን በመድፈኞቹ ቤት በተደጋጋሚ እያሳየ ይገኛል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_02_2018_ዓ_ም

በታደሠ ሙላት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here