ትላንት ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም በስፔን ላሊጋ 4ኛ ሳምንት በሜዳቸው ዲ ሜስታላ ስታዲየም ባርሴሎናን የጋበዙት ቫሌንሲያዎች 5 ለ 0 በኾነ ውጤት ተሸንፈዋል፡፡
የቫሌንሲያ ደጋፊዎችም ከዚህ ከባድ ሽንፈት በኋላ በባለቤቶቹ እና ስሜት አልባ ናቸው ባሏቸው ተጫዋቾች ላይ የበረታ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
በሜዳቸው በባርሴሎና 5ለ0 ከተሸነፉበት አሳፋሪ ውጤት በኋላ በቫሌንሲያ ደጋፊዎች ከፍተኛ ቁጣ የተነሳ ሲኾን በክለቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ውድቀት እና በሜዳ ላይ የታየውን ደካማ አፈፃፀም በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ከስታዲየም ውጭ ተሠባሥበውም ታይተዋል፡፡
አራት ሳምንታት በተጓዘው የስፔን ላሊጋ ቫሌንሲያ የመጀመሪያ ጨዋታዋቸውን በአቻ ውጤት ቢያጠናቅቁም የትላንቱ በባርሴሎና የደረሰባቸው ሽንፈት 3ኛ ተከታታይ ድል አልባ ጉዟቸው ኾኗል፡፡
የሲንጋፖሩ ባለሀብት ፒተር ሊም እና ልጃቸው ኪያት ሊም ባለቤትነት የሚመራው ቫሌንሲያ እያሳየ ያለው ደካማ ውጤት ለተቃውሞው መባባስ ምክንያት ኾኗል፡፡
የክለቡ ደጋፊዎችም መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ካልቻሉ የክለቡ ፕሬዝዳንት ኪአት ሊም እና ዋና የባለአክሲዮን ድርሻ ባለቤቱ ፒተር ሊም ክለቡን ለቀው እንዲወጡ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ “ወደ ቤታችሁ ሂዱ” የተቃውሞው መሪ መልዕክት ነበር፡፡ ይህ ተቃውሞ በባለቤቶቹ ላይ ብቻ አይደለም ስሜት አልባ ናቸው ባሏቸው የተወሰኑ ተጫዋቾችም ላይ ጭምር እንጂ፡፡
ጨዋታውን ለመከታተል ወትሮውኑ ስታዲየም ቀድመው የሚገኙት ደጋፊዎቹ ለ19 ያህል ደቂቃዎች በመዘግየት ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
በ2025 ግንቦት ወር ላይ ወደ ፕሬዝዳንትነት ጭምር የመጡት ኪያትም ሊም ጨዋታውን ስታዲየም ተገኝተው መከታተል የቻሉ ሲኾን በቀጥታ ተቃውሞውንም ለመታዘብ ችለዋል፡፡
በአራት የላሊጋ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠራቸው በክለቡ ላይ እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ የሚያሳይ ሲኾን ቡድኑን በላሊጋ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ አስቀምጦታል።
እንደ ፈረጆቹ ዘመን በወርሐ ታኅሳስ 2024 ወደ አሠልጣኝነት መንበሩ የመጡት ካርሎስ ኮርቤራ ከአርቡ የሴቪያ ጨዋታ በፊት ይሄንን የሚረብሽ ስሜት ማርገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



