በስፔን ባስክ ግዛት በሳን ሰባስቲያን የባሕር ዳርቻ አሸዋማ ስፍራ በባዶ እግር ኳስ በመጫወት የተጠነሰሰ የታሪክ ምዕራፍ።
ሚኬል አርቴታ እና ዣቪ አሎንሶ ገና የዘጠኝ ዓመት ሕጻናት እያሉ በአንቲጉኦ ወጣት ክለብ ውስጥ በአንድነት ሲጫወቱ ህልማቸው አንድ ነበር ለሚወዱት ክለብ ሪያል ሶሲዬዳድ አብረው መጫወት።
ከዓመታት በኋላ ግን የሕይወት መንገድ ለያይታቸው አርቴታ የባርሴሎናን ላ ማሲያን ሲቀላቀል አሎንሶ ደግሞ በሶሲዬዳድ በኩል የከፍታ መንገዱን ጀመረ።
ሆኖም ያ በሕጻንነታቸው የተሳሰረው የወዳጅነት ገመድ እና የእግር ኳስ ፍቅር በጭራሽ አልተበጠሰም።
እንግሊዝን መዳረሻ አድርገው አሎንሶ ለሊቨርፑል ሲፈርሙ አርቴታ ደግሞ ወደ ከተማ ተፎካካሪው ኤቨርተን አቀኑ።
በሜዳ ላይ የመርሲሳይድ ደርቢ ባላንጣ ቢኾኑም በሊቨርፑል ከተማ ውስጥ በአንድ ሕንፃ ጎን ለጎን እየኖሩ እራት አብረው የሚበሉ፣ ስለ እግር ኳስ ታክቲክ ሲወያዩ የሚያመሹ ነበሩ።
ሦሥት አስርት ዓመታትን የተሻገረው ወዳጅነት
ዛሬ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በለንደን ሀያላን ክለቦች ለታላቅ መድረክ ተፋጠዋል።
በሚኬል አርቴታ ይበልጥ የተቀናጀው የሻምፒወኑ አርሰናል ጥብቅ የታክቲክ ሥርዓት እና በዣቪ አሎንሶ የሚመራው የቸልሲ ፈጣን እና ማራኪ የእግር ኳስ ፍልስፍና ሲገናኙ ለተመልካች ድንቅ የእግር ኳስ ድግስ ይፈጥራል።
እንደ ብረት የጠነከረው እና በውድድር ዓመቱ እስካሁን መረቡን ያላስደፈረው የአርቴታ ጥብቅ የተደራጀ መከላከል የምዕራብ ለንደኑን ክለብ አደገኛ የፊት መስመር ለመቁረጥ ወደ ሜዳ ይገባል።
በአጭር ቅብብሎሽ ተቃኝቶ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተቃራኒ ቡድንን መረብ በተደጋጋሚ የሚደፍረው የዣቪ አሎንሶ ሥብሥብ የኢምሬትስ ስታዲየሙን ፍልሚያ ተናፋቂ ያደርገዋል።
በተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር ከተለመደው የሜዳ ላይ ፍልሚያ ባለፈ የሁለት አብሮ አደግ ድንቅ አሠልጣኞች የታክቲክ እና ፍልስፍና ፍጥጫን ዛሬ ምሽት 12፡30 ያስመለክተናል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም
በታደሠ ሙላት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



