ከካርሎ አንቸሎቲ መልቀቅ በኋላ ያልተሳኩ ሙከራወችን ያደረገው ማድሪድ አዲስ የአሸናፊነት መንፈስ ገንብቷል። የቀድሞ ተጫዋቾቹን ዣቪ አሎንሶን እና አልቫሮ አርቤሎአን በአሠልጣኝነት ሞክሮ አልሳካለት ቢል የቀድሞ አሠልጣኙን አምጥቷል።
ጆዜ ሞሪንሆ በቤርናባው ትልቅ መነቃቃት መፍጠራቸውን ባለፉት ሦሥት ጨዋታዎች ተመልክተናል። ባለፉት ሦሥት የላሊጋ ጨዋታወች 10 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የአጥቂ ክፍል በአድካሚው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ አልዛለም። ኬልያን ምባፔ፣ ቪኒሽየስ እና ጁድ ቤሊንግሀም በየሀገሮቻቸው መለያ ዓለም ዋንጫው ላይ አድካሚ ጉዞ ቢያደርጉም በክለባቸው ተሳትፎ ወኔያቸው ጠንክሯል።
የሎስ ብላንኮወቹ የኋላ ክፍልም በሦሥት ጨዋታ ሁለት ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት። በቦታው ኢብራሂማ ኮናቴ እና ማርክ ኩኩሪያ ለመላመድ አልተቸገሩም።
ተጋጣሚያቸው ሪያል ቤቲስ ባለፈው ሳምንት ሳይጠበቅ በሌቫንቴ አምስት ግብ ተቆጥሮበት መሸነፉ ለማድሪዱ ጨዋታ ይበልጥ እንዲጠነቀቅ ያደርገዋል።
ሪያል ማድሪድ ለዚህ ጨዋታ እየተዘጋጀ ባለበት አንድ እንግዳ ድንገተኛ ጉብኝት አድርጎ ነበር። የቀድሞ አሠልጣኙ ካርሎ አንቸሎቲ። የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኙ ወደ ማድሪድ ተመልሰው ጆዜ ሞሪንሆ እና ተጫዋቾችን አነቃቅተው ተመልሰዋል።
“ጥሩ መነቃቃት አይቻለሁ” ብለዋል ዶን ካርሎ። የሪያል ቤቲስ እና ሪያል ማድሪድ ጨዋታ የ4ኛ ሳምንት የላሊጋ መክፈቻ መርሐ ግብር ኾኖ ላ ካርቱሃ ስታዲየም ላይ ምሽት 4፡00 ሲል በአርቢትር አሊሃንድሮ ሄርናንዴዝ ፊሽካ ይጀምራል።
በግርማ ሞገስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



