የስፔን ላሊጋው ሻምፒዮን ባርሴሎና ቤልጄማዊውን ወጣት የክንፍ መስመር ተጫዋች ጄሲ ቢሲውን ለማዛወር ከክለብ ብሩጅ ጋር ከስምምነት ላይ ደርሷል።
ታዋቂዎቹ የስፖርት ጋዜጠኞች ማትዮ ሞሬቶ እና ፋብሪዚዮ እንዳረጋገጡት ከኾነ ተጫዋቹ ወደ ባርሴሎና ለመዘዋወር ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ደርሷል።
በቅርቡ ወደ ካታሎኒያ በማምራት የሕክምና ምርመራውን እንደሚያደርግ እና ይፋዊ የውል ስምምነት ፊርማውን እንደሚያስቀምጥ ተነግሯል። ባርሴሎና ለዝውውሩ 10 ሚሊዮን ዩሮ ለክለብ ብሩጅ ይከፍላል።
ወጣቱ የክንፍ መስመር ተጫዋች በቤልጄየሙ ክለብ ብሩጅ የወጣት ቡድን ውስጥ አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት የባርሴሎናን የምልመላ ቡድን ትኩረት መሳብ እንደቻለ ነው የተገለጸው።
የካታሎኑ የእግር ኳስ ቡድን ባርሴሎና በሃንሲ ፍሊክ መሪነት ከማላሲያ አካዳሚ ፍሬዎች በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ ለቡድኑ ፕሮጀክት የሚኾኑ ወጣት እና ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾችን ለማሠባሠብ ጥረት ላይ ይገኛል። የጄሲ ቢሲው ፊርማም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መኾኑ ነው የተገለጸው።
የ18 ዓመቱ ታዳጊ ፊርማውን ካኖረ በኋላ የባርሴሎና ሁለተኛ ቡድን የኾነውን ባርሳ አትሌቲክን እንደሚቀላቀል ያሆ ስፖርት አስነብቧል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



