“አፍሪካ የዓለም ዋንጫን የምታነሳበት ጊዜ ቅርብ ነው” ካፍ

0
74

 

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ በአፍሪካ ሀገራት የተመዘገበው ታሪካዊ ውጤት አፍሪካ የዓለም ዋንጫን የማንሳት ህልሟ እውን የሚኾንበት ጊዜ መቃረቡን እንዳመለከተ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሞትሴፔ ተናግረዋል።

በ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር ከተሳተፉት 10 የአፍሪካ ሀገራት መካከል 9ኙ ከምድብ ጨዋታ ምዕራፍ አልፈው ወደ 32ቱ ዙር በመግባት 90 በመቶ ስኬት ማስመዝገባቸውን የገለጹት ዶክተር ሞትሴፔ ይህም በውድድሩ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የማለፊያ ምጣኔ መኾኑን ጠቁመዋል።

በውድድሩ ሞሮኮ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፏ ትልቅ አድናቆት የተቸራት ሲኾን ግብጽም እስከ 16ቱ ሀገራት መድረሷ ተገልጿል። አልጄሪያ፣ ኬፕቫርዴ፣ ኮትዲቯር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋና፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱንዝያ ያሳዩት ድንቅ ብቃትም ለአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ጥንካሬ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተመላክቷል።

ካፍ ይህንን ስኬት ለማስቀጠል እና በ2030 ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን፣ የቴክኒክ ሠራተኞችን እና የእግር ኳስ ባለሙያዎችን የሚያሰባስብ ጉባኤ እንደሚያዘጋጅ ተነግሯል።

እንደ ሊደር ሽፕ ኦርግ መረጃ በሁሉም 54 አባል ሀገራት የወጣቶች እግር ኳስ ልማት፣ የአሠልጣኞች ትምህርት እና የሀገር ውስጥ ሊጎች ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንደሚደረግ የገለጹት ዶክተር ሞትሴፔ ሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች እና ክለቦች የፊፋ እና የካፍ ደረጃዎችን የጠበቁ ስታዲየሞች በመገንባት የሜዳ ላይ ጨዋታዎቻቸውን በሀገራቸው ውስጥ ማካሄድ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

#AMICO #ስፖርት #2030WorldCupAfrica

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ16_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here