በፈረንጆቹ ጥቅምት 11/2026 የሚካሄደው 48ኛው የቺካጎ ማራቶን አሸናፊዎችን ለመገመት አዳጋች እና እጅግ ፉክክር የተሞላበት እንደሚኾን የውድድሩ አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል።
በውድድሩ የኡጋንዳው አትሌት ያኮብ ኪፕሊሞ እና ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ፈይሳ የታዋቂ አትሌቶችን ዝርዝር ይመራሉ።
በሴቶች ዘርፍ የባለፈው ዓመት ቺካጎ ማራቶን አሸናፊ የኾነችው እና 2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ በመግባት ድል የቀናት ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ፈይሳ ክብሯን ለማስጠበቅ ወደ ውድድሩ ትመለሳለች።
ከእሷ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ሁለተኛ የወጣችው መገርቱ አለሙ፣ ሱቱሜ ከበደ፣ ደጊቱ አዝመራው እና ፋንቱ ወርቁ ለድል ከሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በሌላ በኩል የቀድሞዋ የዓለም ሪከርድ ባለቤት እና የሁለት ጊዜ የቺካጎ ማራቶን አሸናፊ ብሪጂድ ኮስጊ ከ2019 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ የምትሳተፍ ሲኾን 2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ በማስመዝገብ በሰዓት የዝርዝሩን ቀዳሚነት ይዛለች።
የቦስተን እና የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊዋ ኬንያዊቷ ሻሮን ሎኬዲም በቺካጎ መድረክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
በወንዶች ምድብ ባለፈው ዓመት በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ አሸናፊ የኾነው የኡጋንዳው ያኮብ ኪፕሊሞ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። ኬኒያውያኑ አሞስ ኪፕሩቶ እና አሌክስ ማሳይ ለድል ከሚጠበቁ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች መካከል ናቸው።
በኢትዮጵያ በኩል የ2024 የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ሚልኬሳ መንገሻ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የሚጠበቅ ሲኾን፤ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ታደሰ ታከለ፣ አስራር ኃይርደን እና ቦኪ ድሪባ ሀገራቸውን ወክለው ከሚፎካከሩት ውስጥ ይገኙበታል።
በመጭው ጥቅምት ከ100 በላይ ሀገራት እና ከሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት ይህ ዓለም አቀፍ ውድድር ለአስተናጋጇ ከተማ ከ755 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ እና ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ዓላማዎች ገንዘብ የሚሠበሠብበት መኾኑ ታውቋል።
ከውድድሩ አስቀድሞም ለሦሥት ቀናት የሚቆየው የአቦት ጤና እና አካል ብቃት ኤክስፖ የሚካሄድ ይኾናል።
#አሚኮ #ስፖርት_አትሌቲክስ
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_17_2018 ዓ_ም
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



