ከንጉሣውያን አድናቆት እስከ 2 ሚሊዮን ሕዝብ የዓደባባይ አቀባበል፤ የስፔን ብሔራዊ ቡድን !

0
129
የ2026 የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮናው የስፔን ብሔራዊ ቡድን (ላሮሃ) ወደ ሀገሩ ሲመለስ በዋና ከተማዋ ማድሪድ ታሪካዊ እና ደማቅ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል።
የቡድኑ አባላት ማድሪድ ባራሃስ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ከስፔኑ ንጉሥ ፊሊፔ ስድስተኛ፣ ከንግሥቷ ሌቲዚያ እና ልዕልታቸው ጋር ተገናኝተው የንጉሣዊ ቤተሰቡን ምሥጋና እና አድናቆት ማግኜታቸው ተነግሯል። ቡድኑ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በሚገኙበት የሞንክሎአ ቤተ መንግሥት ይፋዊ የጀግና አቀባበል ሥነ-ሥርዓት እንደተደረገላቸውም አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከንጉሣዊያን ቤተሰቦች እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቆይታ ካደረገ በኋላም ሁለት ሚሊዮን በሚጠጉ ደጋፊዎቻቸው በተጥለቀለቁት የማድሪድ ጎዳናዎች የዓለም ዋንጫውን በመያዝ ጣራው በተከፈተ አውቶቡስ ድሉን አብረው ሲያከብሩ ታይተዋል።
2 ሚሊዮን በሚጠጋው ሕዝብ ፊት ከያዙት ዋንጫ ባለፈ “እኛ የዓለም ሻምፒዮን ነን” የሚል ቲሸርት በመልበስ ያደረጉትን ተጋድሎ እና ያሳኩትን ድል አስረግጠው አሳይተዋል። ተጫዋቾቹ በየተራ ወደ መድረኩ እየወጡም ለደጋፊው ስሜታቸውን አጋርተዋል።
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ሀሳባቸውን የገለጹት አሠልጣኝ ዴ ላፎንቴ “እነዚህ ተጫዋቾች በዓለም ላይ ካሉ ማናቸውም ተጫዋቾች የተለዩ እና ምርጦች ናቸው። የዓለም ምርጦችም ናቸው። ይህ ድል ይገባቸዋል” በማለት የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች ድንቅ ብቃት አወድሰዋል።
“ዋናው ጥንካሬያችን ማንም ሊበግረው የማይቻለው አንድነታችን እና እርስ በርስ ያለን መተማመን ነው” በማለትም ቡድኑ በውድድሩ ያሳየውን አንድነት አድንቀዋል።
ዴ ላፎንቴ እንደ ላሚን ያማል፣ ፔድሪ፣ ፓው ኩባርሲ ያሉ ወጣት ባለተሰጥኦዎች እንዳሉት በመጥቀስም “የስፔን እግር ኳስ የወደፊት ተስፋ አስተማማኝ እጆች ላይ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
አሠልጣኝ ዴ ላፎንቴ ቡድኑ ሁልጊዜም የስፔንን ስም እና ክብር በዓለም መድረክ ላይ ከፍ ለማድረግ ጠንክሮ መሥራቱን እንደሚቀጥል ለንጉሣዊያን ቤተሰቦች እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።
ስፔን የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ድል ማሳካት የቻለችው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here