“የእግዜር እጅ ” እና ማራዶና

0
146
አርጀንቲና በ1986 የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ ላይ የለበሰችውን መለያ ለመልበስ ከፊፋ ፈቃድ አግኝታለች ሲል የዘገበው ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ነው ።
አርጀንቲና ይሄንን ከሜዳ ውጪ የምትጠቀምበትን መለያዋን ለመልበስ የፈለገችው በሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ ላይ እነ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ይሄንኑ መለያ ለብሰው እንግሊዝን ከውድድሩ ማሰናበታቸውን ለአሁኖቹ የእንግሊዝ ተጨዋቾችን ለማስታወስ እና የሥነ ልቦና የበላይነትን ለመውሰድ እንደኾነም በስፋት እየተዘገበ ይገኛል።
በ1986 ሜክሲኮ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ላይ የወቅቱ ኮከብ ተጨዋች ዲያጎ ማራዶና የቱኒዚያውን ዳኛ አሊ ዲን ናስር ስህተት ተጠቅሞ በእንግሊዞች መረብ ላይ በእጁ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ማራዶና ለዛች ድንቅ ግቡ “የእግዜር እጅ” የሚል ስያሜ የሰጣት ሲኾን እንግሊዛዊያኑም ከ40 ዓመታት በኋላም ይቺኑ በእጅ የተቆጠረችባቸውን ግብ እያስታወሱ በአርጀንቲናውያን ላይ እግር ኳሳዊ ቂምን ቋጥረው ይገኛሉ።
የዚያን ጊዜዋ የማራዶና አርጀንቲና በሜክሲኮ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ወደ ሀገሯ ይዛ በመብረር ታላቅ ድልን የተቀዳጀችበት ወቅትም ነበር።
አሁን ከ40 ዓመታት በኋላ እንግሊዝ ከአርጀንቲና በግማሽ ፍጻሜው ፍልሚያ ተገናኝተዋል። ሁለቱ ሀገራት ካላቸው የታሪክ እና የፖለቲካ ቁርሾ በተጨማሪ የእግር ኳሱ ዓለም የማይዘነጋው ባላንጣነትም አላቸው።
እንግሊዝ እና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫው ለአምስት ጊዜ ያህል ሲገናኙ እንግሊዝ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ትወስዳለች።
በ1962 በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ እንግሊዝ አርጀንቲናን 3 ለ1 አሸንፋታለች።
በ1966 በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው እንግሊዝ በ1 ለ 0 ውጤት ለፍጻሜው አልፋለች።
እንግሊዝ እና አርጀንቲና በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ሲገናኙ ግን ድሉ ለነማራዶናዋ ሀገር አርጀንቲና ኾኗል። አርጀንቲና እንግሊዝን 2 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ማራዶና ሁለቱንም ግቦች በእንግሊዛውያን መረብ ላይ አሳርፏል።
ማራዶና ከግማሽ ሜዳ አንስቶ የእንግሊዝ ተጨዋቾችን እያታለላቸው ግብ ማስቆጠሩ ሳያንሰው ሁለተኛውን እና የማሸነፊያዋን ግብ ደግሞ በእጁ በማስቆጠር ታሪክ የማይዘነጋው ገድል ፈጽሟል።
በ1998 የዓለም ዋንጫ ደግሞ እንግሊዝ እና አርጀንቲና በ16 ቡድኖች ውስጥ ተገናኝተው ሁለት አቻ በመውጣታቸው የተሰጣቸውን የመለያ ፍጹም ቅጣት ምት አርጀንቲና 4 ለ 3 አሸንፋለች ።
በ2002 ምድብ ማጣሪያ ላይ እንግሊዝ አርጀንቲናን 1 ለ 0 በዴቪድ ቤካም ቅጣት ምት አሸንፋታለች።
በ2026 የዓለም ዋንጫ ደግሞ እንግሊዝ እና አርጀንቲና ለስድስተኛ ጊዜ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተዋል።
አርጀንቲና የዓለም ዋንጫን በ1978፣ በ1986 እና 2022 ለሦስት ጊዜ ወስዳለች። እንግሊዝ ደግሞ በራሷ አዘጋጅነት ካስቀረችው የ1966ቱ ዋንጫ በስተቀር ሌላ ዋንጫ ማግኘት አልቻለችም።
እንግሊዝ ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ለመውሰድ 60 ዓመታትን ያስቆጠረች ሲኾን አርጀንቲና ደግሞ ለአራተኛ ዋንጫዋ የምትፋለመው ከአራት ዓመት በኋላ ነው።
አርጀንቲና አሁንም የምትመራው በ39 ዓመቱ እና በስምንት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ነው። ሜሲ በዚህ ውድድር ብቻ እንኳን ስምንት ግቦችን ማስቆጠሩ ለእንግሊዞች የሥጋት ምንጭ ነው።
እንግሊዛውያኑም ቢኾኑ በሃሪ ኬን እና ጁዲ ቤሊንግሃም እግሮች ተማምነው የፍጻሜውን ጨዋታ ከስፔን ጋር ለማድረግ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሁለቱ ሀገራት ካላቸው የታሪክ እና የፖለቲካ ባላንጣነት ባለፈ በእግር ኳሱ ያላቸው ባላንጣነትም ዛሬ ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ በአሜሪካ የሚያደርጉትን የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ የዓለም ሕዝብ በሙሉ በጉጉት የሚጠብቀው ትዕይንት መኾኑን የፊፋ ድረ ገጽ መረጃ ይጠቁማል ።
ትላንት ፈረንሳይን 2 ለ 0 አሸንፋ ለፍጻሜ ካለፈችው ስፔ ን ጋር ከአርጀንቲና እና ከእንግሊዝ ማን አሸንፎ አሁድ ለሚደረገው የፍጻሜው ፍልሚያ የሚደርስ ይመስላችኋል ?
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here