48 ሀገራትን ይዞ 104 ጨዋታዎችን ለማከናወን የተጀመረው 23ኛው የዓለም ሀገራት እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አሁን አራት ሀገራት እና አራት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተውት የግማሽ ፍጻሜ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
ግማሽ ፍጻሜ ውስጥ የገቡት አራቱ ሀገራት አርጀንቲና፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በፊፋ ወቅታዊ የብቃት መለኪያ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡
እንደ ያሁ ስፖርትስ መረጃ ፊፋ የሀገራትን ወቅታዊ የብቃት ደረጃ ማውጣት ከጀመረበት እ.አ.አ ከ1992 ወዲህ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ሲደርሱ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በሌላ በኩል አራት የቀደምት የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን ሀገራት ግማሽ ፍጻሜ ውስጥ ሲገቡም በውድድሩ ታሪክ የአሁኑ ለሦሥተኛ ጊዜ ብቻ ኾኗል፡፡ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ነገር የተከሰተው በ1970 እና 1990 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ነበር፡፡
ዘንድሮ ግማሽ ፍጻሜ ላይ የሚገኙት አራቱም ሀገራት በዚህ የዓለም ዋንጫ እስካሁን ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዳቸውም ሽንፈት አልደረሰባቸውም፡፡
በተለይ ፈረንሳይ እና አርጀንቲና ስድስቱንም ጨዋታዎች ሲያሸንፉ ስፔን እና እንግሊዝ በምድብ ጨዋታ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር (ስፔን ከኬፕቨርዲ፣ እንግሊዝ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ) በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ይሄው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ዛሬ ሲጀመር ፈረንሳይ ከስፔን ምሽት 4፡00 በአሜሪካ ዳላስ ስታዲየም ይገናኛሉ፡፡
የማጥቃት እና የመከላከል እንቅስቃሴያቸው ምጥጥን የሚታይበት ሁለቱ ሀገራት በዚህ የዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር እና ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተቀመጡ ናቸው፡፡
የአጥቂ መስመሯ ጥንካሬ ጎልቶ የሚጠቀሰው ፈረንሳይ 16 ግቦችን አስቆጥራ የተቆጠሩባት ግቦች ሁለት ብቻ ሲኾኑ 11 ግቦችን ያስቆጠረችው ስፔን በበኩሏ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ የተከላካይ ክፍሏን ብቃት እያስመሰከረች ትገኛለች፡፡
ከአስፈሪው የፈረንሳይ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ኬልያን ምባፔ እና ኦስማን ዴምቤሌ በአንድ የዓለም ዋንጫ ከአንድ ቡድን አምስት እና ከዚያ በላይ ግብ በማስቆጠር በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ ከብራዚሎቹ ሮናልዶ እና ሪቫልዶ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ኾነዋል፡፡
ፈረንሳይ እና ስፔን በታላቅ የውድድር መድረክ ለመጨረሻ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ ላይ የተገናኙት ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የዩሮ 2024 ውድድር ሲኾን በወቅቱ ስፔን 2 ለ 1 አሸንፋ በፍጻሜውም እንግሊዝን በመርታት የውድድሩ ሻምፒዮን መኾኗ ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ሀገራት እስከዛሬ በተለያዩ ውድድሮች 38 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ስፔን 18 ጨዋታዎችን በማሸነፍ የበላይነቱን ስትወስድ ፈረንሳይ 13 ጊዜ አሸንፋ በቀሪ 7 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



