በዓለም ዋንጫ ታሪክ ስፔን እና ፈረንሳይ የተገናኙት በ2006 (16 ቡድኖች ውስጥ ) ለአንድ ጊዜ ብቻ ሲኾን በጨዋታውም ፈረንሳይ 3 ለ 1 አሸንፋ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
ስፔን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስትኾን ግብ ጠባቂዋ እና አምበሏ ኢከር ካሲያስ፣ የመሀል ሜዳ ሞተሮቿ አንድሬስ ኢኔሽታ እና ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ አጥቂዋ ዴቪድ ቪላ፣ ተከላካዮቿ ካርሎስ ፑዮል እና ሰርጂዮ ራሞስ ፈጽሞ የማይዘነጉ ተጨዋቾቿ ነበሩ ።
ስፔን አሁንም ላሚን ያማል፣ ፔድሪ፣ ሮድሪ፣ ኒኮ ዊሊያምስን እና ዳኒ ኦልሞን የመሳሰሉ ኮከቦችን የያዘች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላት ሀገር ናት።
ፈረንሳይ ከቀድሞዎቹ ዚነዲን ዚዳን ፣ቴሪ ኦነሪ፣ ሊላን ቱራም፣ ፋቢያን ባርቴዝ እና ያሁኑ አሠልጣኟ የዚያን ጊዜው የቡድኑ አምበል ዲዲየር ዴሻምፕስን የመሳሰሉ ኮከቦች ነበሯት።
ፈረንሳይ አሁንም ኪሊያን ምባፔ፣ ኦስማን ዴምቤሌ፣ ኦሊሴ፣ ቶሽሚኒ እና ሳሊባን የመሳሰሉ ጠንካራ እግር ኳሰኞችን ይዛለች።
ስፔን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የ2010 የዓለም ዋንጫ ብቸኛውን ዋንጫ ያሳካችው ኔዘርላንድስን 1 ለ 0 አሸንፋ ነው። በወቅቱ የማሸነፊያ ግቧን ያስቆጠረው ተጨዋች ደግሞ አንድሬስ ኢኔሽታ ነበረ ።
ፈረንሳይ በታሪኳ ሁለት የዓለም ዋንጫዎችን አሳክታለች። በ1998 ራሷ ፈረንሳይ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ብራዚልን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳች ሲኾን በ2018 ሩሲያ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫም ክሮሺያን 4 ለ 2 በማሸነፍ ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ድሏን አሳክታለች።
ፈረንሳይ በኳታር በተዘጋጀው የ2022ቱ የዓለም ዋንጫም ከአርጀንቲና ጋር በፍጻሜው ተፋልማ ዋንጫውን በአርጀንቲና ተነጥቃለች።
ፈረንሳዊው የሪያል ማድሪድ የግብ አዳኝ ኪሊያን ምባፔ በ2022ቱ የዓለም ዋንጫ በፍጻሜ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረ ብቸኛው አጥቂ በሚል ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ አስፍሯል ።
ምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫም ስምንት ግቦችን አስቆጥሮ ከአርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ጋር ለኮከብ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ ይገኛል።
ምባፔ በዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪዎች መዝገብ ላይም ስሙን በ20 ግቦች እና ከሜሲ ቀጥሎ በሁለተኛነት አስፍሯል።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን እንደ ቡድን ጥሩ ስብስብ ቢኖራቸውም እንደ ኪሊያን ምባፔ ደምቆ የወጣ ተጨዋች የላቸውም ።
የባርሴሎናው ወጣቱ አጥቂ ያሚን ያማል በየትኛውም ጨዋታ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል ስለመኾኑ በትላልቅ እግር ኳሳዊ መድረኮች ላይ አሳይቷል ።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ ቢኾንም ምባፔን፣ ዴምቤሌን፣ ኦሊሴን፣ ዱዌን እና ሌሎችንም የአጥቂ መሥመር ተጨዋቾችን ግን በቀላሉ ያስቆሟቸዋል ተብሎ አይጠበቅም ።
የዓለም ዋንጫ ታሪክ፣ ውጤቶች እና አሸናፊዎች ከሚለው የፊፋ ድረ ገጽ ባገኘነው መረጃ መሠረት ፈረንሳይ የተሻለ ውጤት እና የአሸናፊነት ግምት የተሰጣት ሀገር ኾናለች።
ዛሬ ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ በሚደረገው ፍልሚያ የትኛው ሀገር ለፍጻሜ አልፎ የእንግሊዝ እና የአርጀንቲናን አሸናፊ ይገጥማል ? የሚለው ጥያቄ የሁሉም እግር ኳስ ወዳድ ጥያቄ ኾኖ ሰዓቱን በናፍቆት ያስጠብቃል። እናንተስ ማን ለፍጻሜው ያልፋል ትላላችሁ?
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



