የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ውድድር በ9ኛ ከተማው ዩጂን ዛሬ ይካሄዳል፡፡

0
61
#አዲስ_አበባ: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም በ2026 በሃይዋርድ ፊልድ የሚከናወነው የፕሪፎንቴን ክላሲክ ዲያመንድ ለ2 ቀናት ይከናወናል።
የዓለማችን ፈጣን አግሮች ለሌላ ውጤት ፍለጋ ዩጅን ሲደርሱ በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይካፈላሉ፡፡ በ2 እና በ1 ማይል ሴቶች፣ በወንድ 1ማይል አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡
እ.ኤ.አ ከ2022 ወዲህ ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪፎንቴን ክላሲክ የሴቶች የ2 ማይል ውድድርንም ያካተተ ይኾናል።
ይህ ውድድር በመጨረሻው በፕሪ ክላሲክ በተካሄደበት ወቅት የብሩንዲዋ ፍራንሲን ኒዮንሳባ 8 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ08 ማይክሮ ሰከንድ በኾነ ሰዓት በመግባት በታሪክ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችበት ነው። ይህም ከዓለም ክብረ ወሰን በግማሽ ሰከንድ ብቻ የዘገየ ነበር።
ከዓመታት በኋላ ውድድሩ ሲመለስም በውድድር ላይ ከሚሳተፉ 14 አትሌቶች መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
የሁለት ማይሉ ውድድር የሁለት ጊዜ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሀገር አቋራጭ አሸናፊ ማርታ ዓለማየሁን፣ ሂሩት መሸሻን እና አለሽኝ ባወቀን ያካትታል።
በተጨማሪም ሚዛን ዓለም፣ አሳየች አይቸው፣ የኔዋ ንብረት እና አይናዲስ መብራቱ ይሳተፋሉ። የኬንያ፣ የእንግሊዝ እና የአሜሪካ አትሌቶችም ይሳተፉበታል፡፡
በ2024 የ3ሺህ ሜትር የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ጥሩ ሰዓት ያላት አለሽኝ ባወቅ የግል ምርጥ ሰአቷ 8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ከ29 ማይክሮ ሰከንድ ነው፡፡
ፍይዝ ኪፕየገን ወደ ዳይምንድ ሊጉ ውድድር በምትመለስበት የ1ማይል ውድድር 4 የኢትዮጰያ አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡
ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ባለፈው ዓመት በፕሪፎንቴን ክላሲክ አስደናቂ የኾነ 3 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ከ68 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ የዓለም ክብረ ወሰን ሰብራ ነበር። አትሌቷ ወደ ሃይዋርድ ፊልድ ስትመለስም ለሌላ ክብረወሰን እንደምትሮጥ ይጠበቃል፡፡
ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን 4ኛዋ ፈጣን የማይል ሯጭ ስትኾን ባለፈው ዓመት በዚህ ርቀት ከ4 ደቂቃ በታች ለመግባት ሙከራ አድርጋ ነበር።
ጸጌ ዱጉማ፣ ሳሮን በርሄ፣ ብርቄ ኃየሎም እና ወርቅነሽ መሰለ በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በዛሬው ውድድርም በሴቶች 3ሺህ ሜትር መሠናክል ውድድር በታሪክ ከስድስቱ ፈጣን ሯጮች መካከል አራቱ ይፋለማሉ።
በ2024 ባስመዘገበችው 9 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ከ39 ማይክሮ ሰከንድ በታሪክ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው የባህሬኗ የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ዊንፍሬድ ያቪ፣ የዓለም አሸናፊዋ ፌይዝ ቼሮቲች፣ የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊዋ ፔሩዝ ቼሙታይ እና በ2022 በዩጂን የዓለም አሸናፊ የነበረችው ኖራ ጄሩቶ፣ የ2017 አሸናፊዋ ኤማ ኮበርን መካተቷ ውድድሩን አራት የዓለም ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ያሉበት ያደርገዋል።
በወንዶች የ2 ማይል ውድድር ላይ ለመሳተፍ የተመዘገበው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት መዝገቡ ስሜ ብቻ ነው።
በሴቶች 100 ሜትር የሦሥት ጊዜ የዓለም አሸናፊዋ ሜሊሳ ጄፈርሰን-ውደን ስትጠበቅ አምና በዚሁ መድረክ አሸናፊ የነበረችው የሀገሯ ልጅ ሻካሪ ሪቻርድሰን ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃታል፡፡ ሁለቱም አትሌቶች ዘንድሮ በተወዳዳሩባቸው ውድድሮች የተሻለ ሰዓት መግባት ችለዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የጃማይካዎቹ መንትዮች ቲያና ቲና ክላይተን፣ ሸሪካ ጃክሰን፣ ኤሚ ኸንት፣ አዳጃ ሆጅና ዲና፣ አሸር-ስሚዝ እና ሌሎችም ተጠባቂ አትሌቶች ናቸው፡፡
በወንዶች 200 ሜትር ከኦስሎው ዳይመንድ ሊግ በኋላ ለሌላ ድል ሌትስሌ ቶቦጎ ዩጅን ደርሷል፡፡ በዕለቱ ተጠባቂ ከኾኑ ርቀቶች መካካል አንዱ የወንዶች 400ሜትር ነው፡፡
ፓሪስ ላይ የዲያመንድ ሊጉን ክብረወሰን የሰበረው የቦትስዋናው ቡሳንግ ኮለን ኬቢናትሺፒን ከአሜሪካዎቹ ራይ ቤንጃሚን እና ኩዊንሲ ሆል ጋር ይፋለማል፡፡
ከእነዚህ ርቀቶች ውጭ በሜዳ ተግባራትም የዩጅን ዲያመንድ ሊግ ይጠበቃል፡፡ ውድድሩ ከምሽቱ 5:20 ጀምሮ ይካሄዳል።
ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here