“የዓመቱ የ2 ማይል ፈጣን ሰዓት አሸናፊ አለሽኝ ባወቅ”

0
60

 

#ባሕር_ዳር ሰኔ 28/2018 ዓ.ም
ከዓለም ዋንጫው በተጨማሪ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የዩጅን ዲያመንድ ሊግ ውድድር ትናንት ተደርጓል። በኦሪገን ዩኒቨርሲቲ ሀይዋርድ ፊልድ ፕሪፎንቴን ክላሲክ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው የዩጅን ዲያመንድ ሊግ ውድድር የዓለም ኮከቦችን አፎካክሮ ፈጣን ሰዓቶች ተመዝግበዋል። የተጠበቁ አትሌቶችም ድል አድርገዋል።

ከ2022 የፈረንጆቹ ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰው የ2 ማይል የሴቶች ውድድር በኢትዮጵያዊቷ አትሌት አለሽኝ ባወቅ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።

አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተካፈሉበት ውድድር የአማራ ማረሚያ ቤት አትሌቲክስ ክለቧ አለሽኝ ርቀቱን ለመጠናቀቅ 9 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ከ02 ማይክሮ ሰከንድ ወስዶባታል። ይሄም የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ኾኗል።

በርቀቱ በ2ቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አለሽኝ ባወቅ እና ሂሩት መሸሻ መካከል የነበረው ፉክክር እስከ መጨረሻ ሜትሮች ድረስ አጓጊ ትንቅንቅ እንድንመለከት ያደረገ ነው።

አለሺኝ የመጨረሻውን ሜትሮች ቀድማ በመውጣት መሪነቱን የያዘች ሲኾን የዓለም ከ20 ዓመት በታች የ3 ሺህ ሜትር ሻምፒዮኗ በቀዳሚነት አጠናቃለች።
ከአለሽኝ በ0.18 ሰከንድ ብቻ ዘግይታ የገባችው ሂሩት መሸሻ 9 ደቂቃ ከ20 ስከንድ ከ20 ማይክሮ ሰከንድ በኾነ ሰዓት ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቃለች።

ከድሉ በኋላ አስተያየቷን የሰጠችው አለሺኝ በጣም ጥሩ ውድድር ነበር” ብላለች። “ውድድሩ ፈጣን አልነበረም ነገር ግን ስላሸነፍኩ በጣም ደስተኛ ነኝ ነው ያለችው። ሰዓታችን የዘገየ በመኾኑ ፍጥነትን ለመጠቀም በመወሰን ፈጣን አጨራረስ ተጠቅሜያለሁ ስትልም ተናግራለች።

ይሄ ሰዓትም የዓለማችን 35ኛው ፈጣን ሰዓት ኾኗል። በዚህ ርቀት መሠረት ደፋር በ2007 ቤልጅየም ላይ ያስመዘገበችው 8 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ከ58 ማይክሮ ሰከንድ የዓለም ክብረወሰን ሲኮን በመቀጠልም ገንዘቤ ዲባባ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ መልክናት ውዱ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ስንታየሁ እጅጉ የፈጣን ሰዓት ባለቤቶች ናቸው።
በፈረንጆቹ 2010 በርሚንግሃም እንግሊዝ ላይ ፈጣን ሰዓት ካስመዘገበች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሰዓት የገባችው አለሽኝ ባወቅ ናት።

ማርታ አለማየሁ 4ኛ፣ የኔዋ ንብረት 7ኛ እና አሳየች አይቸው 8ኛ ኾነው ጨርሰዋል።

ትላንት ከተደረጉት መካከል የ1 መይል ሴቶች ሲኾን ሳሮን በርሄ እና ወርቅነሽ መሰለ 11ኛና 13ተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በርቀቱ የተጠበቀችው እና አምና ክብረወሰን መስበር የቻለችው ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየገን 3ተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አሜሪካዊቷ ኒኪ ሂልትዝ የአሜሪካን ክብረወሰን ስትሰብር የአመቱ ፈጣን ሰአቷም ሆኗል። 4 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ49 ማይከሮ ሰከንድም የገባችበት ሰአት ነው።ሌላኛዋ ኬንያዊት ዶርከስ ኢዎይ 2ኛ ኾናለች።

ለ2 ቀናት ሲካሄድ በአጭር እና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ውድድሩ ተካሂዶበታል።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_የዩጅን_ዲያመንድ_ሊግ

በሐናማርያም መስፍን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here