ብራዚል በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ የበላይነት ቢኖራትም፣ በታሪኳ ኖርዌይን ማሸነፍ ከባድ ኾኖባት ቆይቷል። ሴሌሳኦዎቹ ባለፉት ሁለት ግንኙነቶቻቸው ድል ቀንቷቸው አያውቅም። ዛሬ ምሽት 5፡00 ላይ በኒውዮርክ ኒውጀርሲ ስታዲየም የሚካሄደው ጨዋታም ብራዚል ይህንን ታሪክ የምትቀይርበት ወይስ ኖርዌይ የበላይነቷን የምታስቀጥልበት? የሚለው ትልቅ ትኩረት ስቧል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከ28 ዓመታት በፊት ካደረጉት ብቸኛ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ፊት ለፊት ይገናኛሉ።
በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረገው የማይረሳው ጨዋታ እ.ኤ.አ በ1998 በቬሎድሮም ስታዲየም የተካሄደው ነበር። በወቅቱ ብራዚል 1 ለ 0 እየመራች ብትቆይም፣ በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ በተቆጠሩባት 2 ግቦች በአስቆጭ ሁኔታ መሸነፏ ይታወሳል።
የሚገርመው በወቅቱ ኖርዌይ ብራዚልን ስታሸንፍ በቡድኑ ውስጥ ተጫዋች የነበሩት የአሁኑ የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስታሌ ሶልባከም ናቸው። አሁን ካለው የኖርዌይ ሥብሥብ ውስጥ ያንን ጨዋታ በዕድሜ ሊያስታውስ የሚችለው የ35 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ኦርጃን ኒላንድ ብቻ ነው። ከእርሱ ውጭ ያሉ ዘጠኙ ተጫዋቾች የተወለዱት ያ ታሪካዊ ጨዋታ ከተደረገ በኋላ ነው።
ብራዚል በምድብ ሦስት ስኮትላንድን እና ሄይቲን በማሸነፍ፣ ከሞሮኮ ጋር አቻ በመለያየት ምድቧን በአንደኝነት አጠናቅቃለች። በ32ቱ ዙር ግን ከጃፓን ጋር በነበራት ጨዋታ ተቸግራ በጭማሪ ሰዓት 2 ለ 1 በኾነ ውጤት አሸንፋለች።
ኖርዌይ ደግሞ በምድብ ዘጠኝ ኢራቅን እና ሴኔጋልን በማሸነፍ፣ በፈረንሳይ ብቻ ስትሸነፍ ሁለተኛ ኾና አጠናቅቃለች። በ32ቱ የዙር ጨዋታ የአፍሪካዋን ተወካይ አይቮሪኮስትን በመጨረሻ ደቂቃዎች 2 ለ 1 በኾነ ውጤት በማሸነፍ ነው እዚህ የደረሰችው። ይህ ድል ለስካንዲኔቪያዋ ሀገር ከ1938 እና 1998 በኋላ ያስመዘገበችው የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድል ነው።
በዚህ ተጠባቂ ጨዋታ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡት የብራዚሉ ቪኒሺየስ ጁኒየር እና የኖርዌዩ አርሊንግ ብራውት ሀላንድ ናቸው። ሀላንድ ኖርዌይ በውድድሩ ካስቆጠረቻቸው 10 ግቦች መካከል ግማሹን አምስት ግቦችን አስቆጥሯል። በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎው አሁንም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። የአምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ የቡድኑን አማካኝ ክፍል የመምራት ኀላፊነትም ከፍተኛ ነው።
በካርሎ አንቸሎቲ የሚመራው የብራዚል ሥብሥብ በተለይም በተከላካይ ክፍሉ ላይ ያለውን ክፍተት አስተካክሎ መቅረብ ይኖርበታል። ጣሊያናዊው አሠልጣኝ አንቸሎቲ ኖርዌይ ጥራት ያለው እና ፈታኝ ቡድን መኾኑን ገልጸዋል። የባርሴሎናው የፊት መስመር ተጫዋች ራፊንሀ ሙሉ ለሙሉ ወደ ብቃቱ ባይመለስም በምሽቱ ጨዋታ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ሊጫዎት እንደሚችል ጠቁመዋል።
የኖርዌዩ አሠልጣኝ ሶልባከን በበኩላቸው ጨዋታው የዳዊት እና ጎልያድ ዓይነት ፍልሚያ ቢመስልም ግባቸው ዝም ብሎ መጫወት ሳይኾን ማሸነፍ እና ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ መኾኑን በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
የኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ግምት ብራዚል በመደበኛው የጨዋታ ሰዓት ለማሸነፍ የ53 ነጥብ 6 በመቶ ዕድል አላት ሲል በአንጻሩ የኖርዌይን የማሸነፍ ዕድል 22 ነጥብ 4 በመቶ አድርጎ አስቀምጧል። ይሁን እንጂ የሁለቱም ቡድኖች የተከላካይ ክፍል ድክመት ጨዋታውን እጅግ ተቀራራቢ እና ማራኪ ያደርገዋል ሲል ነው የተነበየው።
በሌላ በኩል ሌሊት 9፡00 ላይ አዘጋጇ ሜክሲኮ ሌላ ፈታኝ ጨዋታ ከእንግሊዝ ጋር ታደርጋለች።
#የአሚኮ_ዜና #ስፖርት
#አዲስ_አበባ: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



