የሻምበል አበበ ቢቂላ የማራቶን ውድድር ነገ በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል።

0
16

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እ.አ.አ 1960 አንድ ታላቅ ሰው የሀገሩን ሰንደቅ አስቀድሞ በባዶ እግሩ ሲሮጥ ታየ። ሮጦም ድል አመጣ።

ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን መላ አፍሪካንም አኮራ። ይህ በደማቅ ቀለም የተጻፈው ታሪክ የተገኘው ሀገሩን እና አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ አስቦ በተሰለፈው ጀግና ነው። ይህ ጀግና ለብዙዎች ሕልም የመሰለውን ገድል ፈጸመው።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1960 በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ማራቶንን ሮጦ የዓለም ክብረወሰን የኾነ ሰአት አስመዝግቦም አሸነፈ። እነኾ ይሄ ከተከናወነ 66 ዓመታት አለፉ።

ይህ ገድል ታዲያ በትውልድ ቅብብሎሽ ቀጥሎ በማራቶን የደመቁ አትሌቶችን አሳይቷል። ይሄ ታሪክ ሌሎችን ለማምጣት የሚያግዝ ሕያው የኾነ ውጤት ነውና።

ለዚህ ታላቅ አትሌት መታሰቢያ ይኾን ዘንድ በስሙ የተሰየመ የማራቶን ውድድር እየተካሄደለት ነው። በእርሱ ስም በተሰየመው እና ለዓመታት በተካሄደው ውድድር በርካቶች ተሳትፈው ድል አድርገዋል። ሀገርን የመወከል እድልም አግኝተውበታል።

በሻምበል አበበ ቢቂላ ስም የማራቶን ውድድሮ ተሰይሞ መከናወን ከጀመረ 41 ዓመታት ተቆጥረዋል። የ42 ኪሎሜትር የማራቶን ውድድሩ ዘንድሮም ሰኔ 21/2018ዓ.ም በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ ይከናወናል። ለበርካቶች የውድድር እድል የፈጠረ ተተኪ አትሌቶች የታዩበት መድረኩ ለ42ተኛ ጊዜ ነው ነገ የሚካሄደው።

ከ12 ክለቦች፤ ከ4 ክልሎች እና ከተማ አሥተዳድሮች የተውጣጡ አትሌቶች በውድድሩ እንደሚካፈሉ ተገልጿል። አንጋፋ አትሌቶች እና የግል ተወዳዳሪዎችም ተፎካካሪ ኾነው ይቀርቡበታል ተብሏል።

ለውድድሩ 323 ተወዳዳሪዎች ተመዝገበዋል። ካለፈው ዓመት አንጻር የ41 አትሌቶች ቅናሽ የታየበት ይህ ውድድር በተወሰኑ ክልሎች ላይ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች የተሳታፊዎችን ቁጥር እንደቀነሰው ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለአሸናፊ አትሌቶች የሜዳልያ እና የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ዘገቢ:- ሐናማርያም መስፍን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here