እንጅባራ: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንጅባራ ከተማ ከሰኔ 10/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በዘጠኝ ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የ1ኛ ሊግ የክለቦች የእግር ኳስ ውድድር በእንጅባራ ከተማ “ቻሌ ግሻጉም” ክለብ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
ዚገም ወረዳን ከእንጅባራ ቻሌ ግሻጉም ጋር ያገናኘው የዋንጫ ጨዋታ መደበኛው 90 ደቂቃ ያለ ግብ ተጠናቅቆ በፍጹም ቅጣት ምት ቻሌ ግሻጉም 3 ለ 1 በኾነ ውጤት አሸናፊ ኾኗል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ ውድድሩ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለሦሥት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያነቃቃ መኾኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃው ክልላዊ የክለቦች ውድድር ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወክለው የሚወዳደሩ ጠንካራ ተወዳዳሪ ክለቦችን መለየት የተቻለበት መኾኑንም ገልጸዋል።
ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ ስፖርተኞች፣ የስፖርት አፍቃሪያን፣ የከተማው ነዋሪዎች እና የጸጥታ አካላትም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር ዳግም መጀመሩ በናፈቁት ሜዳ እንዲዝናኑ እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ የውድድሩ ታዳሚዎች ናቸው።
ስፖርት አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለማጽናት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል። መሠል ስፖርታዊ ውድድሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ነው ያሉት።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



