ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት መካሄድ ይጀምራሉ። ብራዚልን ከስኮትላንድ የሚያገናኘው ጨዋታ ሌሊት 7:00 ላይ በሃርድ ሮክ ስታዲየም ይካሄዳል።
ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላቸውን ዕድል የሚወስን በመኾኑ ከፍተኛ ጉጉትን ፈጥሯል።
በአሠልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ የሚመሩት ብራዚሎች በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሞሮኮ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ በሁለተኛው ጨዋታ ሃይቲን 3 ለ 0 አሸንፈው ነጥባቸውን 4 ማድረሳቸው ይታወሳል።
በታሪኳ የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያን አልፋ የማታውቀው ስኮትላንድ ዛሬ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ወደ ሜዳ ትገባለች።በመጀመሪያው ጨዋታ ሃይቲን 1 ለ 0 ያሸነፉት ስኮትላንዶች በሁለተኛው ጨዋታ በሞሮኮ 1 ለ 0 በኾነ ጠባብ ውጤት ተሸንፈዋል።
በዚህ ምድብ በተመሳሳይ ሌሊት 7:00 ላይ ሞሮኮ ከሃይቲ ይጫወታሉ።
ከእነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ምሽት 4:00 ላይ ቦስኒያ ከኳታር እና ስዊዘርላንድ ከካናዳ ይጫወታሉ።
የዓለም ዋንጫ የምድብ አንድ ተጠባቂ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሌሊት 10:00 ላይ ሲደረጉ ሜክሲኮ ከቼክ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ኮሪያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ጨዋታቸውን እንደሚያካሂዱ ቢቢሲ አስነብቧል።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት
በሳሙኤል ጥሩነህ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



