የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገራት ጉዞ ሲፈተሽ።

0
68
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮውን ሳይጨምር እስከ ዛሬ ከተካሄዱት 22 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች መካከል ከአንድ በላይ በኾኑ ሀገራት በጣምራ የተስተናገደው እ.አ.አ በ2002 ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ላይ የተካሄደው መድረክ ብቻ ነው፡፡
የዘንድሮው 23ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ከሁለትም በላይ በሦሥት ሀገራት ጥምረት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ የጋራ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሦሥቱ ሀገራት ኳታር ላይ በተካሄደው ያለፈው የ2022 የዓለም ዋንጫ ውድድር ማጣሪያውን አልፈው ተሳትፈው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በአስተናጋጅነታቸው በቀጥታ ያለ ማጣሪያ አልፈው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
እነዚሁ ሦሥት ሀገራት ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ከማስተናገድ ባለፈ በሜዳቸው እና ሰፊ ቁጥር ባላቸው ደጋፊዎቻቸው ፊት ውጤታማ የመኾን ከባድ ኀላፊነት ተሸክመዋል፡፡
የውድድሩ የኋላ ታሪክ እንደሚያስረዳው የዓለም ዋንጫን ያስተናገዱ ሀገራት ጥሩ የሚባል የውጤታማነት ጉዞ አላቸው፡፡
እስካሁን ከተካሄዱት 22 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ስድስት አስተናጋጅ ሀገራት (ኡራጓይ 1930፣ጣሊያን 1934፣እንግሊዝ 1966፣ምዕራብ ጀርመን 1974፣አርጀንቲና 1978 እና ፈረንሳይ 1998) ሻምፒዮን በመኾን ዋንጫውን ሀገራቸው ላይ አስቀርተዋል፡፡
ሁለት ሀገራት (ብራዚል 1950፣ ስዊድን 1958) ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ ሦሥት ሀገራት ደግሞ (ቺሊ 1962፣ ጣሊያን 1990፣ ጀርመን 2006) ሦሥተኛ ደረጃን በማግኜት ለሜዳሊያ በቅተዋል፡፡
ስምንት አስተናጋጅ ሀገራት በበኩላቸው ቢያንስ ከምድባቸው አልፈው እስከ አራተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ገብተዋል፡፡
እንደ ያሁ ስፖርትስ መረጃ የዓለም ዋንጫን አስተናግደው ከምድብ መርሐ ግብር ማለፍ ያልቻሉ ሦሥት ሀገራት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ስፔን 1982፣ ደቡብ አፍሪካ 2010 እና ኳታር 2022 ሲኾኑ የ1982ቱን የተለየ የሚያደርገው በወቅቱ ውድድሩ ሁለት ምዕራፍ የምድብ ማጣሪያ ኖሮት ስፔን ሁለተኛው ዙር ላይ የተሰናበተች መኾኑ ነው፡፡
የአሁኑ ውድድር ጣምራ አስተናጋጆችስ ጉዟቸው እስከምን ድረስ ይኾናል የሚለው በ38 ቀናት የውድድሩ ቆይታ የሚታይ ቢኾንም አጀማመራቸው ግን መልካም ይመስላል፡፡
በመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸው ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 0፣ አሜሪካ ፓራጓይን 4 ለ 1 ሲረቱ ካናዳ ከቦስኒያ 1 ለ 1 አቻ ተለያይተዋል፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here