ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጽያ የካፍን መመዘኛ የሚያሟላ ስታዲየም በመጥፋቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ ማድረግ የሚገባውን ጨዋታ ከሀገሩ ውጭ ለማድረግ ተገድዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ሀገር ለመመለስ ስታድዬም ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው። እየተገነቡ ከሚገኙ ስታድዬሞች መካከል የባሕር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም አንደኛው ነው።
ስታዲየሙ አሁን ላይ የካፍን መስፈርት አሟልቶ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጋሻው ተቀባ ሰታዲየሙ 90 በመቶ ግንባታው መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
ሜዳው ካፍ የሰጠውን አስተያየት በመከተል የመጫወቻ ሜዳ ሳር፤ የክብር እንግዶች መቀመጫ፤ የተጫዋቾች መልበሻ ክፍል፣ የሜዳው መብራቶች እና ሌሎች ሥራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ኾነው ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።
ሜዳው አሁን ባለው የግንባታ ፍጥነት ከቀጠለ በመጭው መስከረም ለሚኖረው የአፍረካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ይደርሳል ነው የተባለው፡፡
የካፍ ገምጋሚ ቡድንም የስታዲየሙን ሥራ ይጎበኛል ተብሎም ይጠበቃል።
ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ ውብ የኾነችው ባሕር ዳር ከተማ ካላት ድምቀት በተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ እና የስፖርቱ ቱሪዝም ማዕከል እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



