ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ።
ምሽት 2:00 ላይ በፖርቱጋል እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ይጠበቃል።
ጨዋታው አዳዲስ ታሪኮች የሚመዘገቡበት እንደኾነም ይጠበቃል። በአንድ በኩል የፖርቱጋል የእግር ኳስ ፈርጥ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስድስተኛ የዓለም ዋንጫ ጨዋታውን የሚጀምርበት ይኾናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከ52 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ ውድድር የተመለሰችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርግበት ነው።
ጨዋታውን ከአጥቂው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባሻገር እንደ ቡሩኖ ፈርናንዴዝ፣ ቪቲኒሃ እና ጃኦ ኔቬስ ዓይነት የመሃል አማካዮችን በስብስቧ የያዘችው ፖርቱጋል በቀላሉ እንደምትቆጣጠረው የብዙዎች ግምት ነው።
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ልምድ ያላቸውን እንደ አሮዋን ዋን ቢሳካ እና አክሴል ቱዋንዘቤ ያሉ ተከላካዮች ያሏት ኮንጎ ቀላል ተጋጣሚ እንደማትኾንም ይጠበቃል።
በእግር ኳስ ዘመኑ ከመረብ ያገናኛቸውን ግቦች 1 ሺህ ለማድረስ እየታተረ የሚገኘው የ41 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በምሽቱ ጨዋታ ግብ ያስቆጥር ይኾን የሚለው ጉዳይም በእግር ኳስ ተመልካቹ ዘንድ ሌላኛው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።
ሮናልዶ ከበረኛ ውጭ በውድድሩ የሚሳተፈው በዕድሜ ትልቁ ተጫዋች በመኾንም ክብረ ወሰኑን የሚይዝ ይኾናል።
በሌላ የምሽት መርሐ ግብር፦
👉 ኢንግላንድ ከ ከክሮሺያ ምሽት 5:00 ላይ
👉 ጋና ከፓናማ ሌሊት 8: 00 ላይ እና
👉 ኡዝቤኪስታን ከኮሎምቢያ ንጋት 11: 00 ላይ ይጠበቃሉ።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



