እያነጋገረ የሚገኘው የኖርዌይ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን መልዕክት አዘል ፎቶግራፍ !

0
27

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኖርዌይ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለ2026ቱ የሰሜን አሜሪካ ዓለም ዋንጫ ጉዞ ከመነሳቱ በፊት ከታዋቂው ብሪታኒያዊ ዴቪድ ያሮው ጋር በመኾን ያደረጋቸው እነዚህ የፎቶ ሥብሥቦች በዓለም ዙሪያ ያሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን ቀልብ ስበዋል። ፎቶወቹ ሦሥት ቢኾኑም የትርጉም ጥልቀታቸው ግን ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

የቫይኪንግ ጭብጥ ያለው ታሪካዊ ፎቶ ኖርዌይ ከ28 ዓመታት ረጅም ጥበቃ በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ማለፏን ተከትሎ ታሪካዊ ማንነታቸውን ለማሳየት የተነሱት ድንቅ ፎቶ ነው። እንደ ኤርሊንግ ሃላንድ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ያሉ 26ቱም ተጫዋቾች በኦስሎ የባሕር ዳርቻ ላይ ሙሉ የቫይኪንግ ጋሻ፣ ሰይፍ እና ባሕላዊ ልብስ ለብሰው ከበስተጀርባቸው ጥንታዊ የቫይኪንግ መርከቦችን አሰልፈው የታዩበት ነው።

ምስጢሩም ልክ አባቶቻቸው ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አሜሪካ እንደተጓዙት ሁሉ አሁንም ይህ ወርቃማ ትውልድ አሜሪካ ላይ ክብርን ፍለጋ “መርከብ እየቀዘፉ” መኾናቸውን ያሳያል።

ሌላው ፎቶ እጅግ ማራኪው ብሔራዊ ማሊያ ሲኾን ኖርዌይ ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያዘጋጀችው ማሊያ የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት እና የሰሜናዊውን ተፈጥሮ ውበት ባማከለ መልኩ የተሠራ ሲኾን ተጫዋቾቹ ማሊያውን ለብሰው የተነሱት የቡድን ፎቶ የዘመናችን እጅግ ውብ እና ማራኪ የስፖርት ፎቶግራፍ ተብሎ ተወድሷል።

ሌላው ፎቶ የስኬት መነሻን ማስታወስ የቻለ ነው። ይህኛው ደግሞ ከሁሉም በላይ ልብ የሚነካ እና እግር ኳስን “ተራ ጨዋታ” ከመኾን በላይ የሚያደርግ ሀሳብ ነው። እያንዳንዱ ተጫዋች ዛሬ ያለበትን ታላቅ ደረጃ (እንደ ማንቸስተር ሲቲ ወይም አርሰናል) ሳይኾን በልጅነቱ እግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመረበትን የአካባቢውን ትንሽ ክለብ ማሊያ ለብሰው በጋራ የተነሱት ፎቶ ነው።

ይህ ፎቶ ተጫዋቾቹ ዛሬ በዓለም መድረክ ላይ ቢደምቁም፣ የመጡበትን ማኅበረሰብ በጎ ፈቃደኝነትን እና መነሻቸውን መቼም እንደማይረሱ የሚያሳይ የጋራ አንድነት መግለጫ ነው።

ኖርዌይ ከሜዳ ውጭ ባሳየችው በዚህ ድንቅ የፈጠራ ጥበብ እና የባሕል ኩራት የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ገና ሳይጀምር በደመቀ ሁኔታ አስጊጠዋለች።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_እግር_ኳስ

በጥበቡ ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here