ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ነገ በታላቅ ድምቀት በሚጀመረው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ አሸናፊው ሀገር የዋንጫ ባለቤት ከመኾኑም ባለፈ 50 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በ48 ሀገራት መካከል ይደረጋል። ከእነዚህ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ዋንጫውን ለማንሳት እነማን ቅድመ ግምት አገኙ?
👉 ፈረንሳይ፦ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ለዋንጫው ከታጩት ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቅሷል። አሁን በዓለም እግር ኳስ ላይ አስፈሪው እና ጥልቅ ሥብሥብ ያለው ቡድን ነው ይላል የዘጋርዲያን ዘገባ። የኪሊያን ምባፔ መሪነት፣ በአማካይ እና በተከላካይ መስመር ላይ ያለው የተጫዋቾች ጥራት ቡድኑ ለዋንጫ እንዲገመት አድርጎታል።
👉 በዚህ የዓለም ዋንጫ ሌላው ቅድሚያ ግምት ካገኙት መካከል የሚጠቀሰው የአርጀንቲና ቡድን ነው። የ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኑ አርጀንቲና ዋንጫውን በማንሳት ክብሩን ያስቀጥላል የሚል ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ቡድኑ ልምድ እና ወጣትነትን ያቀናጀ ከመኾኑም በላይ አሁንም በሊዮኔል ሜሲ መሪነት እና በጠንካራ ሥብሥብ የተገነባ በመኾኑ ለዋንጫው ዋና ተፎካካሪ እንደኾነ ነው ቅድመ ግምት የተሰጠው።
👉 የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን፦ እንግሊዝ በዓለም ዋንጫው ላይ ካሉት ውድ ስብስቦች አንዱን ይዛለች። እንደ ቤሊንግሃም እና ሃሪ ኬን ያሉ የአውሮፓ እግር ኳስ ኮከቦችን ያሠባሠበው ይሄ ቡድን ካለፉት ውድድሮች ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ ለታሪካዊ ስኬት ይበቃል የሚል ግምት አግኝቷል።
👉 የብራዚል ብሔራዊ ቡድንም ሌላኛው ለዋንጯ የተገመተ ቡድን ነው። ምንም እንኳን በቅርብ ጊዜያት ወጥ አቋም ለማሳየት ቢቸገሩም እንደ ቪኒሲየስ ጁኒየር ያሉ በሪያል ማድሪድ ቤት ደምቀው የታዩ የፊት መስመር ኮከቦች ስላሏቸው እስከ መጨረሻው የመጓዝ ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ታምኗል።
በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ እግር ኳስ እጅግ ሚዛናዊ እና ተሰጥኦ የሞላበት ሥብሥብ አለው የሚባለው የፖርቱጋል ብሔራዊ ቡድንም በአሜሪካ፣ ሜክሲኮና ካናዳው ዝግጅት የመድመቅ ግምትን አግኝቷል። በባለልምድ እና በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ይሄ ሥብሥብ አዲሱን የጥሎ ማለፍ ረጅም መንገድ ተጉዞ ዋንጫው ላይ ለመድረስ ሙሉ አቅም አለው ተብሏል።
👉 የውድድሩ ሌላኛወቹ ድምቀቶች የስፔን እና ጀርመን ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተፎካካሪዎች ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአውሮፓ እግር ኳስ ኀያላኑ ስፔን በወጣቱ ላሚን ያማል መሪነት እና ጀርመን ደግሞ በታክቲክ በበሰለ ስብስቧ በአዲሱ 104 ጨዋታዎች በሚካሄደው ረጅም የውድድር ጉዞ ውስጥ እስከ ግማሽ ፍጻሜ እና ፍጻሜ የመድረስ ከፍተኛ ዕድል እንደሚኖራቸው ተጠብቋል።
ሳይጠበቁ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ፦ አፍሪካውያን በተለይም ሞሮኮ እና ናይጄሪያ አስደናቂ ጉዞ ሊኖራቸው ይችላል። ባለፈው የዓለም ዋንጫ ታሪክ የሠራችው ሞሮኮ አሁንም በጠንካራ ሥብሥብ የምትገኝ ሲኾን ናይጄሪያም በአጥቂ መስመር በያዘቻቸው አስፈሪ ኮከቦች አማካኝነት የአፍሪካን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሊያሳዩ ይችላሉ ተብለው ግምት ካገኙ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ኾነዋል።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_የዓለም_ዋንጫ🇪🇹
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



