ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሊጀመር ቀናት ብቻ በቀረው የ2026 ዓለም ዋንጫ ለይ ለመሳተፍ የኢራን ብሔራዊ ቡድን ሜክሲኮ ገብቷል።
በሰሞነኛው የአሜሪካ እና የኢራን የፖለቲካ ትኩሳት እና ወታደራዊ ውጥረት ምክንያት በውድድሩ ላይሳተፍ ይችላል የሚሉ ስጋቶች የነበሩ ቢኾንም የቡድኑ መድረስ ስፖርት ከፖለቲካ በላይ መኾኑን ያሳየበት ሌላው ምዕራፍ ኾኗል።
የዓለም ዋንጫው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦሥት ሀገራት ማለትም በአሜሪካ፣ በካናዳ እና ሜክሲኮ የሚስተናገድ ሲኾን የኢራን ጨዋታዎች መጀመሪያ በአሜሪካ መሬት ላይ እንዲደረጉ መርሐ-ግብር ወጥቶላቸው ነበር።
ምንም እንኳን በቪዛ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ ምክንያቶች ጨዋታዎቹ ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወሩ ቢደረግም ቡድኑ በውድድሩ ላይ እንዲሳተፍ መደረጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጥረቶችን ለማርገብ ስፖርት አሁንም ትልቅ የሰላም ድልድይ መኾኑን ያረጋገጠ ነው።
ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች ደግሞ አሜሪካ ቪዛ መፍቀዷን ኤንቢሲን ጠቅሶ ኤሲፒኤን የዜና ወኪል አስነብቧል።
ኢራን በምድብ 6 ከቤልጄም፣ ግብጽ እና ኒውዝላንድ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። ይህ ሥብሥብ ሀገሪቱን ከተለያዩ አህጉራት እና የተለየ የፖለቲካ አሰላለፍ ካላቸው ሀገራት ጋር የሚያገናኛት በመኾኑ በባሕል እና በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለቀጣናዊ ሰላም አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚዲያ እና የወታደራዊ ቃላት ጦርነት ቢበረታም የኢራን ስፖርተኞች በታላቁ የዓለም መድረክ ላይ መገኘታቸው የዓለምን ትኩረት ከጦርነት አዋጅ ወደ ስፖርታዊ ፉክክር እና ጨዋነት እንዲዞር ያደርገዋል።
ይህ መድረክ ሀገራት በጦር ሜዳ ሳይኾን በስፖርታዊ ጨዋነት ሜዳ ላይ ተገናኝተው ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ነው።
የኢራን ብሔራዊ ቡድን በቱርክ የነበረውን ዝግጅት አጠናቅቆ ሜክሲኮ መግባቱ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የፖለቲካ ልዩነቶች ሳይበግሩት ዓለምን በሰላም እና በእግር ኳስ ፍቅር የማገናኘት ታላቅ ዓላማውን ከወዲሁ ማሳካት መጀመሩን ያሳያል።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_እግር_”ኳስ
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



