በራስ ላይ የተቆጠሩ ግቦች በዓለም ዋንጫ መድረክ ሲታወሱ !

0
58

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከስምንት ዓመታት በፊት ሩሲያ ባስተናገደችው የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ከተቆጠሩት 170 ግቦች ውስጥ 12ቱ በራስ ላይ የተቆጠሩ ነበሩ። ይህም በ1998ቱ ውድድር ተመዝግቦ የነበረውን የ5 ግቦች ክብረወሰን ከእጥፍ በላይ የሠበረ ኾኗል። ከእነዚህ 12 ግቦች መካከል አምስቱ የጨዋታ ውጤት ቀያሪ የነበሩ ሲኾን የመጀመሪያውን የሞሮኮው አዚዝ ቡሃዱዝ በኢራን ጨዋታ ላይ አስቆጥሯል።

ይህ ሂደት እስከ ፍጻሜው የዘለቀ ሲኾን ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ 2 አሸንፋ ሻምፒዮን በኾነችበት ጨዋታ የክሮሺያው ማሪዮ ማንዱዚች በራሱ ላይ አስቆጥሯል። ማንዱዚች በዓለም ዋንጫ ታሪክ በፍጻሜ ጨዋታ በራሱ ላይ ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ተጫዋች ነው። በአንጻሩ በተከታዩ የ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ በራስ ላይ የተቆጠሩት ግቦች ሁለት ብቻ ነበሩ።

እስከዛሬ በተደረጉ 22 የዓለም ዋንጫዎች ከተቆጠሩት 2 ሺህ 720 ግቦች ውስጥ 54ቱ በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው።

ሜክሲኮ ተጫዋቾቿ አራት ጊዜ በራሳቸው ላይ በማስቆጠር በአሉታዊ ታሪክ ቀዳሚነቱን ይመራሉ።

ፈረንሳይ ተቃራኒ ቡድኖች 6 ጊዜ በራሳቸው ላይ አስቆጥረውላት በመጠቀሟ ተጠቃሚዋ ቀዳሚ ሀገር ናት።

በ1994ቱ የዓለም ዋንጫ የኮሎምቢያው ተከላካይ አንድሬስ ኢስኮባር ከአሜሪካ ጋር በነበረ ጨዋታ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ ምክንያት ወደ ሀገሩ ሲመለስ በታጣቂዎች በጥይት ተደብድቦ የሕይወት ዋጋ ከፍሏል ይህም የማይረሳው አሳዛኝ ክስተት ኾኖ ይታወሳል።

እንደ ያሆ ስፖርት ዘገባ በአንጻሩ በዓለም ዋንጫ ታሪክ በራስ ላይ ምንም ግብ ያልተቆጠረባቸው አራት መድረኮች 1934፣ 1950፣ 1958 እና 1990 ብቻ መኾናቸው ይታወሳል።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_እግር_ኳስ

በኃይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here