ዛሬ ከኢትዮጲያ ጋር የወዳጅነት እና የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚያደርገው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ሲፈተሽ ፤

0
51
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጲያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በ ወዳጅነት እና የ አቋም መለኪያ ጨዋታ ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት ጨዋታወችን ያደርጋል። በአሠልጣኝ ዮኋንስ ሳህሌ እየተመሩ ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔን በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ ውስጥ የገቡት ዋልያወቹ ወደ መደበኛ የነጥብ ጨዋታወች ከመግባታቸው በፊት ዛሬ እና የፊታችን ማክሰኞ በድሬዳዋ ስታዲየም የሚገጥሙት የማላዊ ብሄራዊ ቡድን ምን ይመስላል የሚለውን እንዳስስ።
የማላዊ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በቅፅል ስማቸው “ዘ ፍሌምስ” ወይም “እሳቶቹ” ታሪክ የጀመረው ሀገሪቱ ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ ሲኾን፣ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በአህጉሪቱ መድረክ ላይ ብዙም የሚታወቁ አልነበሩም። ነገር ግን ማላዊ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ በምሥራቅ እና በደቡብ አፍሪካ መገናኛ ላይ የምትገኝ በመኾኗ፣ በሁለቱም ቀጣናዊ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የራሷን የጨዋታ ማንነት መገንባት ጀመረች።
በተለይ በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተጋባዥ ኾና በመጫወት እ.አ.አ በ1978፣ 1979 እና 1988 ዋንጫውን ሦሥት ጊዜ ማንሳት የቻለች ሲኾን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በደቡባዊ አፍሪካ የሀገራት ውድድር ላይ በቋሚነት የምትሳተፍ ብርቱ ተፎካካሪ ናት።
ማላዊ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ ተሳትፋ ባታውቅም፣ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ግን ስሟን በኩራት የጻፈችባቸው ሦሥት ትልልቅ የታሪክ ምዕራፎች አሏት። እ.አ.አ በ1984 እና 2010 በውድድሩ ላይ የቀረቡ ሲኾን፣ በተለይ በ2010 የአንጎላ አፍሪካ ዋንጫ ላይ በወቅቱ ጠንካራ የነበረችውን አልጄሪያን 3 ለ 0 በኾነ አስገራሚ ውጤት በማሸነፍ መላውን አፍሪካ አስደምመው ነበር።
ነገር ግን የቡድኑ ታላቁ እና ታሪካዊው ስኬት የተመዘገበው እ.አ.አ በ2021 በካሜሩን በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር። “እሳቶቹ” በምድብ ጨዋታቸው ዚምባብዌን አሸንፈው፣ በኋላም የአፍሪካ ሻምፒዮን ከኾነችው ጠንካራዋ ሴኔጋል ጋር 0 ለ 0 በመለያየት በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 16ቱ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ማለፍ ቻሉ። ምንም እንኳ በ16ቱ ውስጥ በሞሮኮ 2 ለ 1 በኾነ ጠባብ ውጤት ተሸንፈው ቢወጡም፣ ያሳዩት ድንቅ የሜዳ ላይ ትግል ግን የአፍሪካን እግር ኳስ ቤተሰብ ትኩረት የሳበ ነበር።
እንደ ፊፋ ዶት ኮም መረጃ ቡድኑ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ለ ደቡብ አፍሪካው ሪቻርድ ቤይ የሚጫወተው አጥቂው ጋባዲንሆ ምሀንጎ በ2021 አፍሪካ ዋንጫ ላይ በሞሮኮ መረብ ላይ ከሩቅ ርቀት ያስቆጠራት ድንቅ ቮሊ ግብ ለዓመቱ ምርጥ ግብ እጩ እስከመሆን አድርሷታል።
🇲🇼⚽
በጥበቡ ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here