የስፖርት አካዳሚው ብቃታቸውን እያጎለበተላቸው መኾኑን ሠልጣኝ ወጣቶች ተናገሩ።

0
41
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የየጁ ፍሬ ስፖርት አካዳሚ በወልድያ ከተማ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመት በላይ ኾኖታል። አካዳሚው በወልድያ ስፖርት ክለብ ተጫዋች በነበሩት ሽመልስ ደሳለኝ እና አረፋይኔ ሙሉጌታ ነው የተመሠረተው።
አካዳሚውን በቁጭት መመሥረታቸውንም ለአሚኮ ገልጸዋል። የቁጭታቸው ምንጭ በኘሪምየር ሊጉ የነቃ ተሳትፎ የነበረው ወልድያ ስፖርት ክለብ አሁናዊ ሁኔታ መኾኑን ነው የገለጹት።
በስፖርት አካዳሚው ወልድያን ብሎም ኢትዮጵያን የሚወክል ብቁ ተጫዋች የማፍራት ህልም ሰንቀው አካዳሚውን እንዳቋቋሙት ነው የገለጹልን።
አካዳሚው ከስድስት እስከ 17 ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን አቅፎ እያሠለጠ ሲኾን እንደ ዕድሜያቸው ተገቢ ሥልጠና እየሰጡ መኾኑንም ነው ያስረዱት።
አሁኑ ላይ በአካዳሚው ከ170 በላይ ታዳጊዎችን አቅፈው እያሠለጠኑ ሲኾን ክረምት ላይ ቁጥራቸው ይጨምራል ብለዋል። በወልድያ ስፖርት ክለብ ተጫዋች የነበሩ ስፖርተኞች በማሠልጠን ሂደቱ ላይ አብረዋቸው እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
ወልድያ ከተማ ካላት የታዳጊ ብዛት አኳያ ተጨማሪ አካዳሚዎች ሊኖሩ እንደሚገባም መክረዋል።
የአካዳሚው አሠልጣኝ ዳዊት ፈንታው በአካዳሚው ብቃቱን ማዳበር እንደቻለ ገልጿል። በዚህም በሀገር አቀፍ ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ቡድንን ለመቀላቀል መመረጡን እና ጥሪ እየተጠባበቀ መኾኑን ነግሮናል።
ሌላኛው ታዳጊ ሠልጣኝ ሲራጅ አደም፣ በሚሰለፉበት መስመር እና በዕድሜያቸው ልክ ተገቢውን ሥልጠና እየተሰጡ መኾኑን ገልጿል።
በሥልጠናው ብቃት እና ክህሎቱም እንዲሻሻል ማድረጉን ነው ያስረዳው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here